በክልሉ በሕገ-ወጥ መንገድ የተወረረ 58 ሄክታር መሬት ማስመለስ ተችሏል

86

ሀዋሳ ፤ ጥቅምት 03/2014 ዓ.ም (ኢዜአ)  በክልሉ  በሕገ-ወጥ መንገድ የተወረረ  58 ሄክታር መሬት ማስመለስ መቻሉን የሲዳማ ክልል ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ አስታወቀ።

ቢሮው በ2013 በጀት ዓመት አፈፃፀምና የተያዘው የስራ ዘመን  የትኩረት አቅጣጫ ላይ ያተኮረ የውይይት መድረክ ከባለድርሻ አካላት ጋር እያካሄደ ነው።

በቢሮው የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮሴፍ ሀማሮ እንደገለጹት በበጀት ዓመቱ በከተሞች የሚስተዋለውን የመሬት አስተዳደር ክፍተት ለመሙላትና ሕገ-ወጥ አሰራሮችን የመከላከል ስራ እየተካሄደ ነው። 

በዚህም በተሰራው ስራ 58 ሄክታር በሕገ-ወጥ መንገድ የተወረረ መሬት ማስመለስ መቻሉንና  1 ሺህ 723 ሕገ-ወጥ ግንባታዎች እንዲፈርሱ መደረጉን ተናግረዋል።

የመሬት አቅርቦትን ለማሻሻል በተከናወነው ስራ 908 ሄክታር የሚሆን መሬት በጨረታና በምደባ ማቅረብ መቻሉን አመልክተዋል።

በኢንቨስትመንት ስም ተወስደው ለዓመታት ታጥረው በቆዩ መሬቶች ላይ  የኦዲት ሥራ እየተካሄደ  መሆኑንም ጠቁመዋል።

የክልሉ ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ፍስሀ ፊቾላ እንደተናገሩት፤የከተሞችን ሁለንተናዊ እድገት ለማረጋገጥ ምቹ የሆነ ፕላንና የመሬት አስተዳደር እንዲኖር እየተሰራ ነው።

ለአንድ ከተማ መዋቅራዊ ፕላን፣ ለሶስት ከተሞች ስትራቴጂክ ፕላን እንዲሁም ለስምንት ከተሞች መሠረታዊ ፕላን ተሰርቷል።

30 ለሚሆኑ የገጠር አገልግሎት ማዕከላት ደግሞ "ስኬች " ፕላን ተዘጋጅቶላቸዋል ብለዋል።

የክልሉ  ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ በየነ በራሳ ፤የክልሉ መንግስት በከተሞች ሁለንተናዊ እድገት ለማረጋገጥ ሲሰራ መቆየቱን አስታውሰዋል።

ከተሞች እንዲመሩበት የተሰራላቸው ፕላን  የጥራት ችግር ያለበትና ተግባራዊ ለማድረግ አስቸጋሪ እንደነበር ጠቁመው፤ በበጀት ዓመቱ ነባር ፕላኖችን የመከለስና ማስተካከያ የማድረግ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን አስታውቀዋል።

የፕላናቸው ጊዜ ላለፈባቸውና ፕላን ለሌላቸው ከተሞችም ዘላቂ እድገት መሰረት ያደረገ ፕላን እንዲሰራላቸው መደረጉም ተመልክቷል።

በውይይት መድረኩ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች፣ የቢሮው የዘርፍ ኃላፊዎች፣ ባለሙያዎችና የከተማና ወረዳ አስተዳደር አመራሮችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም