ኢትዮ-ቴሌኮም በ22 ከተሞች የ4ጂ ኤል.ቲ.ኢ አድቫንስድ የኢንተርኔት አገልግሎት ጀምሯል

368

አዲስ አበባ፣  ጥቅምት 3/2014(ኢዜአ) ኢትዮ-ቴሌኮም በሁለተኛ ዙር ማስፋፊያ ስራው በ22 ከተሞች ከፍተኛ ፍጥነት ያለው የ4ጂ ኤል.ቲ.ኢ አድቫንስድ የኢንተርኔት አገልግሎት ማስጀመሩን አስታወቀ።

ኩባንያው ለኢዜአ በላከው መግለጫ በመጀመሪያው ዙር ከፍተኛ የዳታ አጠቃቀም በሚታይባቸው 92 ከተሞች የ4ጂ ኤል.ቲ.ኢ አድቫንስድ የሞባይል ኢንተርኔት አገልግሎት ማስጀመሩን ጠቅሷል።

በሁለተኛው ዙር የ4ጂ ኤል.ቲ.ኢ አድቫንስድ አግልግሎት ማስፋፊያ ስራም የዳታ ትራፊክና ፍላጎት መሰረት በማድረግ በ22 ከተሞች አገልግሎት ማስጀመሩን ገልጿል።

ከጥቅምት 2 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ ኩባንያው በደደር፣ ዱብቲ፣ ደባርቅ፣ እስቴ፣ ሸሃዲ፣ ወረታ፣ ጃዊ፣ አዴት፣ ቢቸና፣ ደጀን፣ ሞጣ፣ አሰላ፣ ጎባ፣ ሮቤ፣ ሶደሬ፣ ባቱ፣ ሃላባ፣ ዱራሜ፣ ኮንሶ፣ ሳውላ፣ ሺንሺቾ፣ እና ወራቤ የ4ጂ ኤል.ቲ.ኢ አድቫንስድ አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረጉን ይፋ አድርጓል።

በአሁኑ ወቅትም አጠቃላይ 112 ከተሞችን የ4ጂ ኤል.ቲ.ኢ አድቫንስድ አገልግሎት ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ጠቁሟል።

ከዚህ ቀደም የአገልግሎቱ ተጠቃሚ በሆኑት የደሴ፣ ደብረ-ታቦር፣ ጎንደር፣ ባህር-ዳር፣ ደብረ-ማርቆስ፣ ሎጊያ፣ ሆሳአና፣ ሶዶ፣ አርባ-ምንጭ እና ቡታጅራ ከተሞችም ተጨማሪ የማስፋፊያ ስራ ተከናውኖ ተግባራዊ መደረጉ ተመላክቷል።

የ4ጂ ኤል.ቲ.ኢ አድቫንስድ የላቀ ፈጣን አገልግሎት በመስጠት የደንበኞችን አገልግሎት ዲጂታላይዝ ለማድረግ፣ ምርታማነትን ለመጨመር እና የቴሌኮም ተሞክሮን ለማሳደግ እንደሚያስችል ተገልጿል።

የ4ጂ ኤል.ቲ.ኢ አድቫንስድ አገልግሎት ተግባራዊ በሆኑባቸው ከተሞች የሚገኙ ደንበኞችም የኩባንያው የሽያጭ ማዕከል 3ጂ የነበረው የሲም ካርድ በነፃ ወደ 4ጂ በቅናሽ ለገበያ መቅረቡን አስታውቋል።

የ4ጂ ኤል.ቲ.ኢ አድቫንስድ አገልግሎት የተጫነባቸው የሞባይል ቀፎዎችን፣ 4ጂ የሚቀበሉ ሞባይሎችን፣ ታብሌቶችንና ዶንግሎችን በመጠቀም ወይም በመግዛት ፈጣን የሆነ የኢንተርኔት አገልግሎትን መጠቀም እንደሚቻልም ኩባንያው ጠቁሟል።

የቴሌኮም አገልግሎት መጠቀሚያ መሳሪያ ወይም ይዘት አቅራቢዎችም በመረጃ የበለጸገ ማህበረሰብና ኢኮኖሚ ለመገንባት በዝርጋታ ላይ የሚገኘውን ከፍተኛ ፍጥነት ያለው የሞባይል ኔትወርክ ግንባታ በማገዝ ለህብረተሰቡ በስፋትና በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ጥሪ ቀርቧል።