በምዕራብና ደቡባዊ የአገሪቱ ክፍሎች በሚቀጥሉት አስር ቀናት ዝናብ ያገኛሉ

310

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 3/2014(ኢዜአ) በምዕራብና ደቡባዊ የአገሪቱ ክፍሎች በሚቀጥሉት አስር ቀናት የተለያየ መጠን ያለው ዝናብ የሚያገኙ መሆኑን የብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ አስታወቀ።

ኤጀንሲው ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው በሚቀጥሉት አስር ቀናት በምዕራብና ደቡባዊ የአገሪቱ ክፍሎች የተለያየ መጠን ያለው ዝናብ ሲጠበቅ በጥቂት የደቡባዊ  የአገሪቱ  አጋማሽ የተወሰኑ ቦታዎች  ላይ ደግሞ  ከባድ ዝናብ ሊኖር ይችላል።

በሌላ በኩል ቀሪዎቹ  የአገሪቱ  ክፍሎች በአመዛኙ ደረቅ፣ ፀሐያማና ነፋሻማ የአየር ሁኔታ ይኖራቸዋል ብሏል።

ከኦሮሚያ ጅማ፣ ኢሉአባቦር፣ ሁሉም የወለጋ ዞኖች፣ አርሲና ባሌ፣  ዞኖች፣ የቤንሻንጉል ጉሙዝ ፣ምዕራብ ትግራይ በሚቀጥሉት አስር ቀናት በአብዛኛው ከመደበኛ ጋር የተቀራረበ ዝናብ እንደሚያገኙ ይጠበቃል።

ከአማራ ክልል የሰሜንና የደቡብ ጎንደር ዞኖች፣ ምዕራብ ጎጃም፣ የባህርዳር ዙሪያ እና አገው አዊ ተመሳሳይ የዝናብ መጠን ይኖራቸዋል ተብሎ ይገመታል።

ከደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል ወላይታ፣ የከፋና ቤንቺ ማጂ፣ የጌዲዮ፣ የጉራጌ፣ የጋሞና ጎፋ ዞኖች እና ከሱማሌ ክልል ፋፈን፣ ቆራይ፣ ዶሎ እና የሸበል ዞኖች በአብዛኛው ከመደበኛ ጋር የተቀራረበ ዝናብ  እንደሚያገኙም ተጠቁሟል።

በመጀመሪያዎቹ ጥቂት ቀናት ከሚፈጠረው ደመና በሰሜንና ደቡብ ወሎ፣ በሰሜን ምዕራብ፣ በምስራቅ አና ደቡብ ትግራይ፣ በአፋር ክልል ዞን 3 ፣ 4 እና 5  በጥቂት የሰሜን ቦረናና ጉጂ ዞኖች፣ ምስራቅ ሐረርጌ፣ በሐረር፣ በጋምቤላ፣ ደቡብ ኦሞና ሰገን ህዝቦች እንዲሁም በአዲስ አበባ በጥቂት ቦታዎች ላይ አነስተኛ ዝናብ ይኖራል።

የተቀሩት የአገሪቱ ክፍሎች ደረቅ ሆነው እንደሚቆዩ የኤጀንሲው መረጃ አመልክቷል።

በደቡብና ምዕራብ የአገሪቱ  ክፍሎች  የተሻለ እርጥበት  እንደሚኖር ይጠበቃል፤ ይህም ለግብርና ምርት ጠቀሜታ ይኖረዋል ተብሏል።

በምዕራባዊ አጋማሽ የደቡብና ደቡብ ምስራቅ ኢትዮጵያ የአገሪቱ ክፍሎች ያለው ዝናብ ለግብርና ስራ እንቅስቃሴ ጠቀሜታ ይኖረዋልም ተብሎ ይገመታል።

ዘግይተው ለተዘሩትና እድገታቸውን ላልጨረሱት እንዲሁም በተለያየ የእድገት ደረጃ ላይ ለሚገኙ ሰብሎችና ለቋሚ ተክሎች የውሃ ፍላጎት ያሟላል ተብሎ ይጠበቃል።

በአብዛኛው ባሮአኮቦ፣  የደቡባዊና የምዕራባዊ አጋማሽ አባይ፣ የላይኛው አዋሽ፣ የላይኛውና መካከለኛ ኦሞጊቤና ስምጥ ሸሎቆ፣ የላይኛውና መካከለኛ ዋቢ ሸበሌና ገናሌዳዋ ተፋሰሶች እርጥበት እንደሚያገኙ ይጠበቃል።

በመጀመሪያዎቹ ጥቂት ቀናት ውስጥ መካከለኛና ታችኛው  አዋሽ፣ የላይኛው ተከዜ፣ ምስራቃዊ አባይ፣ የታችኛው የገናሌዳዋ፣ ስምጥ ሸለቆ፣ የታችኛው ባሮአኮቦ አና የላይኛውና የመካከለኛው ዋቢ ሸባሌ ተፋሰሶች መጠነኛ እርጥበት መጠን እንደሚያገኙ ይጠበቃል።

የተቀሩት የአገሪቱ ተፋሰሶች ላይ ደረቅና ከፊል ደረቅ ሆነው እንደሚቆዩ መግለጫው አመልክቷል።