የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አዲሱ አደረጃጀት ዓለም አቀፋዊና ጂኦ ፖለቲካዊ ጉዳዮችን ከግምት አስገብቷል

248

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 3/2014  (ኢዜአ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አዲሱ አደረጃጀትና የለውጥ ሥራ ዓለም አቀፋዊና ጂኦ ፖለቲካዊ አካባቢያዊ ጉዳዮችን ከግምት ባስገባ መልኩ መሆኑን ሚኒስቴሩ አስታወቀ።

አደረጃጀቱ ወጪን በመቀነስ ውጤታማ የዲፕሎማሲ ሥራ ለመሥራት ትኩረት ያደረገ መሆኑም ተገልፇል።


በሚኒስቴሩ የአፍሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጀነራልና የተቋሙ የለውጥ ሥራ ኮሚቴ አስተባባሪ አክሊሉ ከበደ፤ ተቋሙን ውጤታማ ለማድረግ የሚያስችል የለውጥ ሥራ መከናወኑን ገልጸዋል።

የለውጥ ሥራው የታለመለትን ግብ እንዲመታና የተቋሙን ቀጣይ አቅጣጫ ለማስቀመጥ የዲፕሎማሲውን ፍኖተ ካርታ የሚያሳይ ዝርዘር ጥናት መካሄዱንም አብራርተዋል።

የተቋሙ የለውጥ ሥራዎች በዋነኝነት በአሰራር፣ በሕግ፣ በአደረጃጀት ማሻሻያና በተቋም ባህል ግንባታ ላይ አተኩሮ መከናወኑንም አስረድተዋል።      

የለውጥ ሥራው ከአገሪቱ የ10 ዓመት መሪ እድቅ ጋር የተጣጣመና ይህንኑ አገራዊ እቅድ ሊያስፈጽም በሚችል መልኩ በተቋም ደረጃ ታልሞ መዘጋጀቱንም ጠቁመዋል።

የተቋሙ የአደረጃጀት ለውጥ ክንውን በዋነኝነት ተለዋዋጩን ዓለም አቀፋዊና ጂኦ ፖለቲካዊ አካባቢያዊ ጉዳዮችን ከግምት ባስገባ መልኩ መሆኑን ገልጸዋል።

ከሰሜኑ የአገሪቱ አካባቢ ጋር በተያያዘ የመጣውን የውጭ ጫና እና ችግሩን ተከትሎ ሊመጣ የሚችለውን ምጣኔ ኃብታዊ ተግዳሮቶች ለመቋቋም በሚያስችል መልኩ መካሄዱንም ተናግረዋል።  

የኮሮና ወረርሺኝ ያስከተለውን ምጣኔ ኃብታዊ ጫና ለመመከትም ከዋና መሥሪያ ቤት ጀምሮ እስከ ሚሲዮኖች ሁሉን አቀፍ አደረጃጀት መሰራቱን ጠቁመዋል።

የአደረጃጀት ማሻሻያው መሥሪያ ቤቱ ተልዕኮውን በብቃት ለመፈጸም፣ ወጪ ለመቀነስና ቅንጅታዊ አሰራርን ለማጠናከር ያስችላል ብለዋል።

በአደረጃጀቱ መሠረት በአንዳንድ አገራት የተዘጉ ሚሲዮኖች ከዋና መሥሪያ ቤት አልያም ደግሞ መቀመጫቸውን ሌሎች አገራት ባደረጉ ኤምባሲዎች የሚሰሩ ይሆናል።

አዲሱ አደረጃጀት ወጭን በመቀነስ ውጤታማ የዲፕሎማሲ ሥራ ለመሥራት ትኩረት ያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

በመሥሪያ ቤቱ አዲሱ የለውጥ ሥራ በተመለከተ የተቋሙ ሠራተኞች፣ ዲፕሎማቶችና ተጠሪ ተቋማት ሠራተኞችም ሥልጠና እየወሰዱ መሆኑን ተናግረዋል።

በተቋሙ የለውጥ ሥራዎችና ግቦች ዙሪያ የጋራ መግባባት ለመፍጠርና ስልጠናው አቅማቸውን ለማጎልበት ያስችላልም ነው ያሉት አቶ አክሊሉ።   

የተቋሙን የለውጥ ሥራ ተከትሎ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በቅርቡ የአደረጃጀትና ሌሎች አሰራሮችን ገቢራዊ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል።