ዓለም አቀፍ የሕግ አሰራሮች ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሠራተኞችም የሚሰሩ ናቸው

73

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 3/2014 (ኢዜአ) መንግስታት ዲፕሎማቶችና ዜጎችን ከአገራቸው የሚያስወጡባቸው ዓለም አቀፍ አሰራሮች ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሠራተኞችም የሚሰሩ መሆናቸውን የሕግ ባለሙያው አቶ ቴዎድሮስ ጌታቸው ገለጹ።

የሕግ ባለሙያው ለኢዜአ እንደገለጹት የኢትዮጵያ እርምጃም ዓለም አቀፍ ድንጋጌን ተከትሎ የተከናወነ ነው ።

በመስከረም 2014 ዓ.ም ኢትዮጵያ በውስጥ ጉዳዬ ጣልቃ ገብተዋል ያለቻቸውን ሰባት የመንግስታቱ ድርጅት ሠራተኞች በ72 ሠዓት ውስጥ ከአገር እንዲወጡ ባሳሰበችው መሰረት ከአገር ወጥተዋል።

በድርጅቱ ሠራተኞች ከአገር መውጣት ለሁለት ጎራ የተከፈሉ የሕግ ክርክሮች ሲነሱም ተስተውሏል።

የመጀመሪያው ኢትዮጵያ "የወሰድኩት እርምጃ ዓለም አቀፍ ሕግና አሰራርን የተከተለ ነው" በማለት የገለጸች ሲሆን፤ ሌላው ደግሞ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት "ሠራተኞቼን የማባረር ሕጋዊ መብት የላትም፤ ማባረር /persona non grata/ ለድርጅቱ ሠራተኞች አይሰራም" የሚለው ነው።

የሕግ ባለሙያው ቴዎድሮስ ጌታቸው የሁለት አገራት ግንኙነት ትኩረቱን የሚያደርገው የቪየና ኮንቬንሽን እንዲሁም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ቻርተር ዋነኛ ቁልፍ ሃሳቡ ሉዓላዊነት መሆኑን ገልጸዋል።

ድንጋጌዎቹ አንድ አገር በሌላ አገር ጉዳይ ላይ ጣልቃ መግባት እንደሌለበት በግልጽ እንደሚያስቀምጡም ጠቅሰዋል።

የመንግስታቱ ድርጅት ተቋማትና ሠራተኞች በዚሁ ዓለም አቀፍ የሕግ አሰራር ውስጥ የሚካተቱ  በመሆናቸው የአንድን አገር ሉዓላዊነትና የሚሰሩበትን አገር ሕጎች ማክበር አለባቸው ብለዋል።

ከዚህ አኳያ ኢትዮጵያም በውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ገብተዋል ያለቻቸውን ሠራተኞች ከአገር ማስወጣቷ ዓለም አቀፍ ሕግን የተከተለ እንደሆነ ተናግረዋል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የቪየና ኮንቬንሽን ለዲፕሎማቶች እንጂ ለሠራተኞቹ እንደማይሰራና ኢትዮጵያም የማባረር ስልጣን የላትም ማለቱ ከዓለም አቀፍ ሕግ አንጻር እንደማያስኬድ ነው የሕግ ባለሙያው የገለጹት።

የቪየና ኮንቬንሽን በአገራት መካከል ባለው ግንኙነት ላይ ብቻ የተመሰረተ ነው የሚል መደምደሚያ እንደሌለውና በዛ ላይ ያልተገደበ መሆኑንም ተናግረዋል።

በተባበሩት መንግስታት ቻርተርና የድርጅቱ ዋነኛ እሴት የሆነው ጣልቃ አለመግባት ነው ያሉት አቶ ቴዎድሮስ ተመድ ሠራተኞቹ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ገብተዋል ወይ? የአገሪቷን ሕግ አክብረዋል ወይ? የሚለውን ጉዳይ ማጣራት ነበረበት ይህንን ግን አላደረገም ብለዋል።

በዓለም አቀፉ ሕግ ኢትዮጵያ ሠራተኞቹን ያስወጣችበትን ምክንያት የማብራራት ግዴታ ባይኖርባትም በተወሰነ መልኩም ቢሆን ተሳትፈውበታል ያለቻቸውን ድርጊቶች መግለጿን አመልክተዋል።

ባለፈው ሳምንት በኢትዮጵያ ጉዳይ በተደረገው የተመድ የጸጥታው ምክር ቤት ስብሰባ በድርጅቱ የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ታዬ አጽቀስላሴ ሠራተኞቹ ፈጽመዋል ብለው የዘረዘሯቸው ተግባራት "ዓለም አቀፍ ሕግን የጣሱ ናቸው" ብለዋል።

የተመድ ዋና ፀሐፊ አንቶኒዩ ጉቴሬዝ በስብሰባው አንድ ጊዜ መብት የላችሁም፤ ሌላ ጊዜ የፈጸሙትን ድርጊት አስመልክቶ መረጃ ስጡኝ በማለት ያነሷቸው ሀሳቦች "ወጥነት የሌላቸውና እርስ በእርስ የሚጋጩ የመከራከሪያ ነጥቦች ናቸው" ሲሉ ነው የሕግ ባለሙያው የገለጹት።

አገራት ዲፕሎማቶችንም ሆነ ሌሎች ዜጎችን ከአገራቸው የማስወጣት እርምጃዎች ዓለም አቀፍ የሕግ አካል እየሆኑ እንደሚመጡና ወደተለመዱ ሕጎች /customary law/ እንደሚያድጉም ተናግረዋል።

ከዚህ በፊትም አገራት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሠራተኞችን ያስወጡባቸው ማሳያዎች መኖራቸውን፤ እነዚህ እርምጃዎች ሲለመዱ ዓለም አቀፍ አሰራር እየሆኑ መምጣታቸውን አስረድተዋል።

በእነዚህ ተግባራዊ እየሆኑ ባሉ ዓለም አቀፍ ሕጎች መሰረት ኢትዮጵያ ሠራተኞቹን ማስወጣቷ ተቀባይነት ያለው ሲሆን፤ ተመድ ያቀረባቸው ሀሳቦች ሕጋዊ ድጋፍ የሌላቸው ናቸው ብለዋል አቶ ቴዎድሮስ።

በሚሰራበት የዓለም አቀፍ ሕግ ትርጓሜ ለዲፕሎማቶች የሚሰሩ ድንጋጌዎች ለተባበሩት መንግስታት ሠራተኞችም የሚሰሩ መሆናቸውን አመልክተዋል።

ዲፕሎማቶችና የዓለም አቀፍ ድርጅት ሠራተኞች የኢትዮጵያን ሕግና አሰራር ተከትለው ስራቸውን ማከናወን እንዳለባቸው አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም