የከተማ አስተዳደሩ በህልውና ዘመቻው ላይ ሙያዊ አገልግሎት ለሚሰጡ ለ40 የጤና ባለሙያዎች ሽኝት አደረገ

130

ጥቅምት 3/2014 (ኢዜአ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በህልውና ዘመቻው ላይ ለሚገኘው የሀገር መከላከያ ሰራዊትና ልዩ ኃይል ሙያዊ ድጋፍ ለሚሰጡ ለ40 የጤና ባለሙያዎች ሽኝት አደረገ።

ከተማ አስተዳደሩ ከተለያዩ ሆስፒታሎች ለተውጣጡ እና ሙያዊ ድጋፍ ለሚያደርጉ የጤና ባለሞያዎች ለ7ኛ ጊዜ ሽኝት ማድረጉን አስታውቋል።

የጤና ባለሞያዎቹ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዮሐንስ ጫላ እና በቢሮው ምክትል ኃላፊ ዶክተር ሙሉጌታ እንዳለ እንዲሁም የቢሮው ማኔጅመንት አባላት በተገኙበት ሽኝት ተደርጎላቸዋል።

የጤና ባለሙያዎች በህልውና ዘመቻው ላይ ሙያዊ አገልግሎት በማድረግ የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እያበረከቱ መሆኑም ተገልጿል።

የጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዮሐንስ ጫላ በሽኝቱ ወቅት እንደገለጹት በሀገሪቱ የተቃጣውን አደጋ ለመመከት በህልውና ዘመቻ ለተሰማራው የመከላከያ ሰራዊትና ልዩ ኃይል የጤና ባለሙያዎች በሙያቸው እያደረጉ ያለው አስተዋጽኦ በምንም ሊተካ እንደማይችል ገልጸዋል።

የጤና ቢሮ ኃላፊው “የጤና ባለሞያዎች ሙያው የሚጠይቀውን ሁሉ አገልግሎት ለመስጠት በመወሰናችሁ ምስጋና ይገባችኋል” ብለዋል።

አክለውም “ቢሮውም ሆነ ከተማ አስተዳደሩ ሁሌም ይኮራባችኋል፤ ከጎናችሁ በመሆንም አስፈላጊውን ድጋፍ ይደረጋል” ሲሉ መናገራቸውን ከአዲስ አበባ ጤና ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።