የህብረተሰቡን የልማት ጥያቄ ለመመለስ ወጪን በመቆጠብ ገቢን ማሳደግ እንደሚገባ ተመለከተ

59
አሶሳ ነሀሴ 11/2010 በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የህብረተሰቡን የልማት ጥያቄ ለመመለስ ወጪን ቆጥቦ ገቢን ማሳደግ ላይ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ተመለከተ፡፡ በክልሉ የ2011 በጀት አጠቃቀም ላይ ውይይት ተካሄዷል፡፡ የውይይት መድረኩን የመሩት የክልሉ ገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ሙፍቲ መርቀኒ እንዳሉት ክልሉ ከፌደራል መንግስት በድጎማ የሚያገኘውና በራሱ የሚሰበስበው ገቢ እየጨመረ መጥቷል፡፡ " ይሁንና እያደገ የመጣውን የህዝቡን የልማት ጥያቄ ለመመለስ በሚደረግ ጥረት ወጪያችን ጨምሯል"ያሉት  አቶ ሙፍቲ  ወጪን ለመመጠን መፍትሄ ያሏቸውን አቅጣጫዎች አመላክተዋል፡፡ ወጪን መቆጠብ፣ የተለጠጠ የገቢ እቅድ ተግባራዊ ማድረግና የቁጠባ ባህልን ማጠናከር  ካመላከቷቸው አቅጣጫዎች መካከል ይገኙበታል፡፡ ''ከክልል እስከ ወረዳ መስሪያ ቤቶች የተካሄደው በጀት አደላደል የክልሉን ወቅታዊ ሁኔታ የሚያሳይ መረጃን መሠረት በማድረግ ነው'' ብለዋል፡፡ አንዳንድ ቢሮዎች ለመደበኛም ሆነ ለካፒታል ስራዎች በጀት እንዲመደብ ወጪያቸውን አስቀድመው እንዲያቀርቡ ሲጠየቁ በወቅቱ ምላሽ እንደማይሰጡ አስረድተዋል፡፡ ፍላጎታቸውን ዘግይተው ቢያሳውቁም በጀትን በማዟዟር ምላሽ ለመስጠት እንደተሞከረ ጠቁመዋል፡፡ አስቀድመው ፍላጎታቸውን በማሳወቅ በጀት ቢለቀቅላቸውም በወቅቱ ሳይጠቀሙ በበጀት ዓመቱ መጨረሻ የሚሯሯጡ ቢሮዎች እንዳሉም ምክትል ኃላፊው ተናግረዋል፡፡ በክልሉ የሰው ኃይል ቅጥርና አመዳደብ በጥናት ላይ ተመስርቶ ተግባራዊ መደረጉን ያመለከቱት አቶ ሙፍቲ "ሆኖም ሁሉም ሠራተኛ ባለው የትምህርት ዝግጅትና ልምድ አቅም አስተዋጽኦ አድርጓል ለማለት አያስደፍርም" ብለዋል፡፡ እርሳቸው እንዳሉት የአቅም ውስንነትና በቁርጠኝነት ማነስ የችግሮቹ ምክያቶች ናቸው፡፡ በአንድ ቢሮ በርካታ የፋይናስ ሠራኞች እያሉ የፋይናስ ዳይሬክቶሬት ካልተመደበ ስራ እስከ ማቆም የሚደርስበት ጊዜ መኖሩን አስታውሰው የሰው ኃይልን በሚገባ በማንቀሳቀስ ስራን ማቀላጠፍ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡ የስራ ሪፖርት በወቅቱ በማያቀርቡ የፋይናንስ ተቋማት ላይ ተገቢውን እርምጃ አለመውሰድ ክፍተት መሆኑን አውስተው በተያዘው የበጀት ዓመት ይሄ ችግር  እንደማይደገም አስታውቀዋል፡፡ የህብረተሰቡን የልማት ጥያቄ ለመመለስ ወጪ ቆጣቢ ገቢ ማሳደግ ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባም አመልክተዋል፡፡ በውይይቱ ከተሳተፉት መካከል የክልሉ ግብርና ቢሮ ባልደረባ አቶ ፀሐይ አዳሙ በበኩላቸው በጀታቸውንና ሥራቸውን አጣጥመው ለመንቀሳቀስ ጥረት እንደሚያደርጉ  ተናግረዋል፡፡ ሆኖም በመስክ ለሚከናወኑ በተለይም የግብርና ሥራዎች ማስፈጸሚያ በጀት አመዳደብ ልዩ ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባም  ጠቁመዋል፡፡ ሌላው የውይይቱ ተሳታፊ አቶ ጋሹ ዱጋዝ  በሰጡት አስተያየት "ወጪያችን በራሳችን ገቢ በመሸፈን ከድጎማ መላቀቅ ይጠበቅብናል" ብለዋል፡፡ በክልሉ መስሪያ ቤቶች በየዓመቱ ሥራቸውን ላለማከናወናቸው በምክንያትነት የሚጠቅሱት የበጀትና የባለሙያ እጥረት ችግር ከነመፍትሄው በጥናት መለየት እንዳለበትም ጠቅሰዋል፡፡ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ለ2011 በጀት ዓመት ማስፈጸሚያ የተመደበው ገንዘብ ከ3 ቢሊዮን 600ሚሊዮን ብር  በላይ  እንደሆነም ተመልክቷል፡፡    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም