የሴቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ማረጋገጥ የሁሉንም ዜጋ ኃላፊነት ይጠይቃል

105

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 01/2014(ኢዜአ የሴቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ለአንድ ወገን ብቻ የሚተው ተግባር ሳይሆን የሁሉንም ዜጋ ኃላፊነት እንደሚጠይቅ የኢትዮጵያ ሴቶች ማህበራት ቅንጅት ገለጸ።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከታዳጊ ሴቶች ጋር በተያያዘ በዋነኝነት በመብቶቻቸው፣ ተግዳሮቶችና በመፍትሄዎቻቸው ዙሪያ ግንዛቤን ማሳደግ እንደሚያስፈልግ በማመን እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር ከጥቅምት 11 ቀን 2ዐ12 ጀምሮ እለቱ በየዓመቱ የዓለም አቀፍ የታዳጊ ልጆች ቀን ሆኖ እንዲከበር መወሰኑ ይታወቃል፡፡

በዚህም የኢትዮጵያ ሴቶች ማህበራት ቅንጅት ቀኑን ዓለም አቀፉ የታዳጊ ሴቶች ቀን "የታዳጊ ሴቶችን ብቃት ማሳደግ እና ሁለንተናዊ ደህንነትን ማረጋገጥ" በሚል መሪ ሃሳብ በዛሬው እለት አክብሯል።

የቅንጅቱ ዳይሬክተር ወይዘሮ ሳባ ገብረመድህን በዚሁ ወቅት ቅንጅቱ 'ማላላ ፈንድ' በተሰኘ ፕሮግራም አማካኝነት በሲዳማ፣ኦሮሚያና አማራ ክልሎች እና በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሀገር አቀፍ የሴት ልጆች የትምህርት ትስስር ዘርግቶ ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

በሀገር ደረጃ ታዳጊ ሴቶችን በመደገፍ ረገድ እየተከናወኑ ያሉ አበረታች ስራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸውም ነው ያነሱት፡፡

ቅንጅቱ የታዳጊ ሴቶች ትምህርታቸውን እንዳያቋርጡ ባለፉት ጊዜያት ትኩረት ሰጥቶ ሲሰራ መቆየቱን አስታውሰው፤ በቀጣይ የታዳጊ የሴቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚከናወኑ ተግባራት ይበልጥ እንዲጠናከሩ እንደሚሰራ ጠቁመዋል፡፡

በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚንስቴር የሴቶች የማካተት ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ዳይሬክተር ወይዘሮ ተስፋነሽ ተፈራ በበኩላቸው የሴቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ለአንድ ወገን ብቻ የሚተው ተግባር ሳይሆን የሁሉንም ዜጋ ኃላፊነት እንደሚጠይቅ ተናግረዋል፡፡

ሚንስቴር መስሪያ ቤቱ ይህን በመገንዘብ ሴቶች በፖለቲካዊ፣ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ መስክ ብቁ እንዲሆኑ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ለአብነትም በስድስተኛው አገራዊ ምርጫ የተሳተፉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ላቀረቧቸው ሴት እጩዎች ተገቢው ደጋፍ እንደተደረገም ገልጸዋል።

የጸጥታ ችግር ባለባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ ሴቶችን በመደገፍ ረገድ እየተከናወነ ያለው ተግባር ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አንስተዋል፡፡

ታደጊ ሴቶች የሚያገኙትን እድል በአግባቡ መጠቀም እንዳለባቸው የተናገሩት ደግሞ የትምህርት ለዘላቂ ልማት ድርጅት ዳይሬክተር ወይዘሮ አምሳለ ሙልጌታ ናቸው።

ታዳጊ ሴቶች በጊዜያዊ ነገሮች ሳይታለሉ ለዓላማቸው ጽኑ እንዲሆኑም መክረዋል፡፡

በማላላ ፈንድ ፕሮግራም እየተደገፉ ያሉ ታዳጊ ሴቶች ፕሮግራሙ በተለይ የትምህርት ግብዓትን በማሟላት ረገድ እያደረገላቸው ላለው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።

ቀኑን በማስመልከት የታዳጊ ሴቶችን ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ምክክር መደረጉን አንስተው፤ ተግባሩ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል፡፡  

ዓለም አቀፉ የታዳጊ ልጆች ቀን በዓለም ለ10ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ለ8ኛ ጊዜ ነው የተከበረው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም