ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ኢትዮጵያንና ህዝቧን በሃቅ በማገልገል ከልመና ለማላቀቅ መስራት አለባችሁ

60

አዲስ አበባ ጥቅምት 01/2014(ኢዜአ)"ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ኢትዮጵያንና ህዝቧን በሃቅ በማገልገል ከልመና ለማላቀቅ መስራት አለባችሁ" ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ገለጹ፡፡

ቀጣይነት ያለው የስራ ልምምድ ካዳበርን ኢትዮጵያን ተረጂ ሳይሆን የምትረዳ አገር ማድረግ እንችላለን ብለዋል።

"አዲስ ምዕራፍ፣ በአገልጋይ መሪነት" በሚል መሪ ሃሳብ አዲስ ለተሾሙ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ስልጠና መስጠት ተጀምሯል።

በስልጠናው ማስጀመሪያ ላይ መልእክት ያስተላለፉት ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ፤ የኢትዮጵያ ህዝብ እና ታላቋን ኢትዮጵያ ለማገልገል እድል የተሰጣችሁ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች እንኳን ደስ ያላችሁ ብለዋል። 

አመራሮች ህዝብን ለማገልግል ባገኙት ታላቅ ዕድል ተጠቅመው ኢትዮጵያን ለማሻገር እና በተግባር የተደገፈ ታሪክ ለመጻፍ መነሳሳት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

የኢትዮጵያን ህዝብ በሚያገለግሉበት ወቅት ከሌብነት ልምምድ ፍፁም ነፃ በመሆን ኢትዮጵያንና ህዝቧን በሃቅ፣ በቅንነት እና በታማኝነት በማገልገል ከልመና ለማላቀቅ መስራት አለባችሁ ብለዋል።

"ኢትዮጵያ ውስጥ በርካታ ትኩረት ያልተሰጣቸው ጉዳዮች አሉ" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሃላፊዎች ከታዩት ይልቅ ወዳልታዩት አተኩሩ ብለዋቸዋል።

አቧራ የለበሱትን በመጥረግ፣ ቋጥኝ የተጫናቸው ሃብቶችን ቋጥኙን በማንሳት ስራ ላይ እንዲውሉ ማድረግ የአመራሩ ዋነኛ ተልዕኮ ሊሆን ይገባል ሲሉ አሳስበዋል።

ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ የተሸፈኑ ነገሮችን በመግለጥና ውብ በማድረግ ኢትዮጵያዊያንን ከስደት ማዳን እንደሚገባ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡

ለአገር ዕድገትና ለህዝቦች ተጠቃሚነት እንዲሰሩ አሳስበው ጠንካራ ስራ በመስራትም ለብልጽግና የማይናወጥ መሰረት መጣል ይጠበቅብናል ነው ያሉት።

ለከፍተኛ አመራሩ በመሰጠት ላይ የሚገኘው ስልጠና ማሳወቅን፣ ማነሣሣትን እና ለቡድን ስራ መዘጋጀትን ዓላማ አድረጎ መዘጋጀቱንም ገልጸዋል፡፡

ከሰልጠናው መጠናቀቅ በኋላም ከአመራሩ የማድረግ ጉጉት፣ ያወቀውን ለመተግበር ቁርጠኛ መሆን እና የዓላማ ጽናት ይጠበቃል ብለዋል።

አዲስ የተሸሙት አመራሮች በተባበረ ክንድ ኢትዮጵያን ወደ ከፍታዋ እንድታመራ ማድረግ ይኖርባቸዋል፤ ለኢትጵያ ብልጽግና መሠረት ለመጣል እንትጋ ሲሉም አስገንዝበዋል።

አመራሩ እጅ ለእጅ ተያይዞ ለጋራ ዕድገትና ብልጽግና መነሣት እንዳለበት ገልጸው ለህዝቦች ተጠቃሚነት መትጋት እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡

ለአምስት ተከታታይ ቀናት በሚሰጠው ስልጠና ሚኒስትሮች፣ ሚኒስትር ዴኤታዎች እንዲሁም የሁለቱ ምክር ቤቶች አፈ ጉባኤዎች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም