በኢትዮጵያ የእዕምሮ ጤና ችግርን ለመፍታት የሁላችንንም ትብብር ይጠይቃል

121

ጥቅምት 1/2014 በኢትዮጵያ የእዕምሮ ጤና ችግርን ለመፍታት ለመንግስት ብቻ የሚተው ባለመሆኑ የሁሉም ትብብር ያስፈልጋል ሲሉ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ዓለሚቱ ኡሞድ ተናገሩ።

የዓለም ጤና እንክብካቤ ቀንን በማስመልከት በሆፕ ፎር ጀስቲስ አሰናጅነት ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ተደርጓል።

በመርሃ ግብሩ ላይ በመገኘት መልእክት ያስተላለፉት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ዓለሚቱ ኡሞድ፤ በኢትዮጵያ የእዕምሮ ጤና ችግርን ለመፍታት የሁላችንም የጋራ ትብብር ይጠይቃል ብለዋል።

የእዕምሮ ጤና ችግርን ለመፍታት የመንግስት ጥረት ብቻውን የሚፈለገውን ውጤት ሊያመጣ እንደማይችል ጠቁመው የሁሉም ጥረት ወሳኝ ነው ብለዋል።

“ከተባበርን የማንሻገረው ችግር ባለመኖሩ የእዕምሮ ጤና ችግርን በዘላቂነት ለመፍታት ሁላችንም በቅንጅት እንስራ” ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።

የሆፕ ፎር ጀስቲስ ካንትሪ ፕሮግራም ዳይሬክተር አቶ ደረጀ ዘለቀ የእዕምሮ ጤና ችግር በአግባቡ መንከባከብ ካልተቻለ ከፍተኛ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ሊያስከትል ይችላል ብለዋል።

በመሆኑም ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት በቂ በጀትና ባለሙያ በማፍራት መስራትን ይጠይቃል ነው ያሉት።

ለዚህም መንግስታዊ እና ያልሆኑ ተቋማት እንዲሁም ሌሎች የጋራ ጉዳይ አድርገው ሊሰሩበት ይገባል ብለዋል።

በተለይ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከትምህርት ጎን ለጎን ግንዛቤ የማሳደግ ሰፊ ስራ እንደሚጠበቅ ነው የተናገሩት።

የሆፕ ፎር ጀስቲስ ጥናት እንደሚያመለክተው በኢትዮጵያ ለአእምሮ ጤና የሚሰጠው ትኩረት አናሳ መሆኑን ይጠቁማል።

ከ100 ሚሊዮን ህዝብ በላይ ባለባት አገር ኢትዮጵያ 100 የማይሞሉ የእእምሮ ጤና ስፔሻሊስት ሃኪሞች እንዳሉ ጥናቱ ያመለክታል።

ለጤና ሴክተር ከሚመደበው ዓመታዊ በጀት ውስጥ ለእዕምሮ ጤና የሚመደበው በጀት 0 ነጥብ 53 ብቻ መሆኑም ተመላክቷል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ በአንድ ቤተሰብ ውስጥ ከሚኖሩ አምስት ሰዎች መካከል አንዱ የአዕምሮ ጤና እክል ችግር ሊያጋጥመው እንደሚችል ይነገራል።

ከኮቪድ-19 መከሰት በኋላ ደግሞ መካከለኛና ዝቅትኛ የሚባለው የድብርትና ጭንቀት መጠን በሶስት እጥፍ መጨመሩን መረጃዎች ይጠቁማሉ።