የፌዴሬሽን ምክር ቤት በቀጣይ በግጭት አፈታትና የህዝቦችን መቀራረብ በሚያጎለብቱ ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርጎ ይሰራል

76

መስከረም 30 ቀን 2014 (ኢዜአ) የፌዴሬሽን ምክር ቤት በቀጣይ በግጭት አፈታትና የህዝቦችን መቀራረብ በሚያጎለብቱ ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርጎ እንደሚሰራ አስታወቀ፡፡

የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ አቶ አገኘሁ ተሻገር ከቀድሞው የምክር ቤቱ አፈ-ጉባዔ አቶ አደም ፋራህ  ጋር በምክር ቤቱ ሲከናወኑ በቆዩ ጉዳዮችና በቀጣይ ትኩረት በሚሹ ዋና ዋና አጀንዳዎች ዙሪያ ተወያይተዋል።

ውይይቱን የተከታተሉት በምክር ቤቱ የአፈ-ጉባኤው የህግ አማካሪ የሆኑት ዶክተር ዘለቀ ተመስገን ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ውይይቱ በአስፈጻሚ እና በህግ አውጪ አካላት መካከል ያለውን ግንኙነት በሚመለከት የወጣው አዋጅን ወደ ትግበራ በሚገባበት ጉዳይ ላይ መክረዋል።

በቅርቡ በተካሄደው ህዝበ ውሳኔ በአብላጫ ድምጽ እንደ አዲስ በሚደራጀው የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ጉዳይ በሚመለከት ውይይት ማድረጋቸውንም ገልጸዋል፡፡

ምክር ቤቱ በህዝበ ውሳኔው መሰረት የሚከናወኑ ተግባራትን በመደገፍ ረገድ የበኩሉን ሚና እንደሚወጣም ነው የጠቆሙት፡፡

ምክር ቤቱ በግጭት አፈታትና ሌሎች የህዝቦችን መቀራረብ በሚያጎለብቱ ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርጎ እንደሚሰራም ገልጸዋል፡፡

"በተጨማሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ካጸደቃቸው አዋጆች ጋር ተያይዘው የሚነሱ ቅሬታዎችን ለመፍታት ይሰራል" ብለዋል።

የፌዴራል መንግስቱ ለክልሎች የሚሰጣቸው የመሰረተ ልማት ስርጭቶችንና ሌሎች ድጎማዎችን በሚመለከት ፍትሃዊነታቸውን የማረጋገጥ ስራ ትኩረት ከተሰጣቸው አጀንዳዎች መካከል መሆኑንም ጠቁመዋል።    

ቅሬታ ይነሳበት የነበረው የፌደራል መንግስቱ ለክልሎች የሚሰጣቸው የመሰረተ ልማት ስርጭቶች ፍትሃዊ መሆናቸውን መቆጣጠር በቀጣይ ትኩረት የሚያገኝ ተግባር እንደሚሆንም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም