ለባህርዳር ከተማ ልማት መፋጠን በስፖርት የዳበረ ወጣት ማፍራት ያስፈልጋል

399

ባህርዳር  መስከረም 30/2014 (ኢዜአ) የባህርዳር ከተማን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ልማት ለማፋጠን በስፖርት አካሉንና አእምሮውን ያበለጸገ ወጣት ማፍራት እንደሚያስፈልግ የከተማው ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ዶክተር ድረስ ሳህሉ ገለጹ።

በከተማ አስተዳደሩና አፍሪካ ንቃ “ዌክ አፕ አፍሪካ” ማህበር አዘጋጅነት ስለ ሰላም ፋይዳ የሚሰብክ የ10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ “እኔ ለባህር ዳር ሰላም እሮጣለሁ” በሚል መሪ ቃል ዛሬ ተካሂዷል።

ዶክተር ድረሥ በሩጫው ማስጀመሪያ ሰነ-ስርዓት ላይ እንዳሉት በባህር ዳር ከተማ ለሰላም የሚተጋ ወጣትን ለመፍጠር የስፖርት ዘርፉን ማነቃቃት ይገባል።

በስፖርት አካሉንና አእምሮውን ያበለጸገ ትውልድ በኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ሁለንተናዊ ልማት በንቃት በመሳተፍ ከተማዋን ለማዘመንና ለኑሮ ተስማሚ ለማድረግ አስተዋጽኦው የጎላ መሆኑን ገልጸዋል።

ከተማዋን ለቱሪዝም ኮንፈረስና ለኢንቨስትመትን የተመቸች ለማድረግም ተከታታይነት ያለው የስፖርት ውድድሮችን በከተማዋ ማዘጋጀት አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።

ለዚህም አፍሪካ ንቃ(ዌክ አፕ አፍሪካ) የተባለው ማህበር ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በመተባበር የተዘጋጀው የ10 ኪሎ ሜትር ሩጫ ወጣቱ ትውልድ ለሰላምና ለስፖርት ትኩረት እንዲሰጥ በማለም ነው።

ወጣቱ ትውልድ በአትሌክስና ሌሎች ስፖርቶች በመሳተፍ ራሱን ከሱስና ሌሎች የጤና ጠንቅ ከሆኑ ድርጊቶች እንዲጠብቅ የጎዳና ላይ ሩጫዎች የሚኖራቸው ፋይዳ የጎላ መሆኑን ተናግረዋል።

አፍሪካ ንቃ የተባለው ማህበር በማረሚያ ቤት ውስጥ ባሉ ወጣቶች ተመስርቶ ዛሬ በባህር ዳር ከተማ የጎዳና ላይ ሩጫ በማካሄድ ወጣቶችን ለማስተማር መብቃቱ የሚበረታታ መሆኑን አስታውቀዋል።

የንቃ አፍሪካ (ዌክ አፕ አፍሪካ) መስራችና ስራ አስኪያጅ ወጣት ታየ ልይህ በበኩሉ ማህበሩ በማረሚያ ቤት ውስጥ በቆየበት ወቅት በታራሚ ወጣቶች የተመሰረተና ማረሚያ ቤት የነበሩ ወጣቶችን በስነ-ምግባር ለማነጽ የተቋቋመ ነው።

የማህበሩ ስያሜም በአፍሪካ አህጉር በየቦታው በሚፈጠረው የሰላም መደፍረስና ግጭት በከንቱ የሚፈሰውን የንጹሃን ደም ለማስቆም ወጣቱን ማስተማር አስፈላጊ ሆኑ በመገኘቱ ነው ብለዋል።

“የአፍሪካ ህዝብ እንደ ቀደምት አባቶቹ ለምን አይነቃም” በሚል ቁጭት ታራሚዎችን ለማስተማርና ለሰላም ዘብ እንዲቆሙ ለማስቻል የተመሰረተና በዚህም ለውጥ ያመጣ ማህበር መሆኑን ገልጸዋል።

እንደ ወጣት ታየ ገለጻ ከፌዴራል ማረሚያ ቤት ወደ ባህር ዳር ማረሚያ ቤት ከተዘዋወረ በኋላም ማህበሩ በእርምት ላይ የነበሩ የባህር ዳር ማረሚያ ቤት ወጣቶችን ሰለሰላም ሲያስተምር ቆይቷል።

“ሰላም አጥብቆ በመመኘት ብቻ አይገኝም” የሚለው ወጣት ባየ ሰላምን በማስፈን የዜጎችን ደህንነት ለመጠበቅ መጀመሪያ ከራስ መጀመር ያስፈልጋል ብሏል።

ለ7 ዓመት በእስር ከቆየ በኋላ በይቅርታ መፈታቱን ጠቁሞ ለመጀመሪያ ጊዜ በባህር ዳር ከተማ የማህበሩን አላማ ያነገበ እስከ 3ሺህ የሚደርስ ህዝብ የተሳተፈበት የጎዳና ላይ ሩጫ ዛሬ ማካሄዱን እንዳስደሰተው ተናግሯል።

በውድድሩ 1ኛ የወጣው የአማራ ፖሊስ አትሌት በረከት ዘለቀ እንደገለጸው እንዲህ አይነት ስለሰላም የሚሰብክ ሩጫ መዘጋጀቱ በክለብ የታቀፉ አትሌቶች የመሮጥ አቅማቸውን ለመፈተሽ የሚያግዝ ነው።

በሩጫው እስካሁን ያደረጉትን ዝግጅት በምን ደረጃ ላይ እንደምገኝ የራሴን አቅም ፈትሼበታለሁ ያለው አትሌት በረከት ላዘጋጁት አካላት ምስጋና አቅርቧል።

በውድድሩ በሁለቱም ጸታ ከ1ኛ እስከ 3ኛ ለወጡ አትሌቶች ከ5ሽህ እስከ 10ሽህ ብር፣ የዋንጫና የእውቅና የምስክር ወረቀት ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።