ጅማ ዩኒቨርሲቲ የካንሰር ህክምና መስጫ ማዕከሉን እንዲያሳድግ ይደገፋል

116

መስከረም 30/2021(ኢዜአ) የጅማ ዩኒቨርሲቲን የካንሰር ህክምና ማዕከል አገልግሎት አሰጣጥ ለማሟላት ለሚደረገው ጥረት መንግስት ተገቢውን ድጋፍ እንደሚያደርግ የጤና ሚኒስትር ዲኤታ ዶክተር ደረጄ ዱጉማ ገለጹ።

ሚኒስትር ዲኤታው በ2 መቶ ሺህ ብር ወጪ የጨረር ህክምና መስጫ ማሽን የገባለትን የካንሰር ህክምና ማዕከል ትላንት ሲጎበኙ እንዳሉት በኢትዮጵያ ውስጥ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች በተለይ የካንሰር ስርጭት እየጨመረ ይገኛል።

የካንሰርን ህመም በመድኃኒት ለመፈወስ በርካታ ሙከራዎች መደረጋቸውን የገለጹት ዶክተር ደረጀ የጨረር ህክምናው የተሻለ ውጤታማ እንደሆነም ተናግረዋል።

“አገልግሎቱ በጅማ መጀመር አዲስ አበባ ድረስ ሕክምናውን ለማግኘት ለሚቸገሩ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ለሚኖሩ ወገኖች ትልቅ ዕድል ነው” ብለዋል።

በመሆኑም በጅማ ዩኒቨርሲቲ የሕክምና ማዕከል የጨረር ህክምና አገልግሎት መጀመሩ የሚደነቅ ነው” ሲሉ ሚኒስትር ዴኤታው ገልጸዋል።

የህክምና ማእከሉ በሙሉ አቅም መስራት እንዲችል ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አስፈላጊውን የመሣሪያና የቁሳቁስ ድጋፍ እንደሚያደርግም ዶክተር ደረጄ ቃል ገብተዋል።

በጅማ ዩኒቨርስቲ የሕክምና ማዕከል የኦንኮሎጂ ስፔሻሊስት ዶክተር አብዩ ለገሰ በበኩላቸው ማሽኑ ለካንሰር ህሙማን የህክምና አገልግሎት የጎላ መፍትሄ የሚሰጥ መሆኑን ተናግረዋል።

በተጨማሪም ለታካሚዎች የተሻለ ሕክምና ለመስጠት የመጠባበቂያ ማሽን ፣ ማሽኑን ለማንቀሳቀስ ጄኔሬተርና ባለሞያዎችን መጨመር አስፈላጊ መሆኑንም ጠቁመዋል።

በጅማ ዩኒቨርሲቲ ጤና ኢኒስቲትዩት ሜዲካል ዶክተር አበበ ዱጉማ ከጨረር ህክምና በስተቀር የኬሞቴራፒ እና የቀዶ ሕክምና አገልግሎት ይሰጥ እንደነበር ገልፀዋል። 

ለዚሁ የጨረር ህክምና የካንሰር ህመምተኞች ወደ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ተልከው ለ2 ዓመታት ያህል በቀጠሮ ሲጉላሉ ይቆዩ እንደነበር አውስተው ይህ ማሽን በጅማ ጤና ኢኒስቲትዩት ውስጥ መገኘቱ ለካንሰር ህመምተኞች ትልቅ ትርጉም አለው ብለዋል።

በአሁኑ ጊዜ የጨረር ህክምና ማሽኑ የሙከራ አገልግሎት እየሰጠ ሲሆን በቀን እስከ 10 ሕሙማንን እያገለገለ መሆኑን ገልጸው በሙሉ አቅሙ ሲሰራ ከዚህ የበለጠ አገልግሎት እንደሚሰጥ አስረድተዋል።