በአስቸጋሪ የኑሮ ሁኔታ የሚገኙ ሴቶችን ህይወት ለመለወጥ በትኩረት እየተሰራ ነው

60

ባህርዳር  መስከረም 30/2014 (ኢዜአ)  በአስቸጋሪ የኑሮ ሁኔታ የሚገኙ ሴቶችን በተለያዩ የሙያ ዘርፎች በማሰልጠንና የስራ ማስጀመሪያ ገንዘብ በመደገፍ ህይወታቸውን ለመቀየር እየሰራ መሆኑን ኢየሩሳሌም የህጻናትና ማህበረሰብ ልማት ድርጅት አስታወቀ።

ድርጅቱ ከቀዳማዊት እመቤት ወይዘሮ ዝናሽ ታያቸው ቢሮ ጋር በመተባበር ለ4ኛ ዙር በተለያዩ ሙያዎች ለሶስት ወራት ያሰለጠናቸውን 35 ተጋላጭ ሴቶችን አስመርቋል።

የድርጅቱ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሙሉጌታ ገብሩ በምርቃቱ ላይ እንዳሉት ድርጅቱ የአገሪቱን ዘላቂ ልማት ለማረጋገጥ በሚያስችሉ የስራ ዘርፎች የመንግስትን ክፍተት እየሞላ ይገኛል።

በዚህም በ22 የአገሪቱ አካባቢዎች በማህበራዊ ዘርፍ በትምህርት፣ በጤና፣ በገቢ ማስገኛ፣ በአቅም ግንባታና በምግብ ዋስትና ማረጋገጥ ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝም ገልጸዋል።

በማህበራዊ አገልግሎት ከሚሰጠው አገልግሎት ውስጥም በከተሞች ተጋላጭ የሆኑ ሴቶችን በመለየት ከአስከፊ አኗኗራቸው በመውጣት ሰርተው የራሳቸውንና የቤተሰባቸውን የኑሮ ሁኔታ እንዲለውጡ ማስቻል ነው።

በዚህም ከቀዳማዊት እመቤት ጽሕፈት ቤት ጋር በመተባበር በ2012 ዓ.ም ጀምሮ 600 ተጋላጭ ሴቶችን ካሉበት የከፋ የአኗኗር ዘይቤ ለማውጣት እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

እስከ አሁንም ዛሬ የሚመረቁትን 35 ጨምሮ 76 የሚሆኑ ሴቶችን የስነ ልቦና፣ የገንዘብ አያያዝና ቁጠባ፣ የስነ ተዋልዶና ሌሎች ስልጠናዎችን በመስጠት የተሟላ ስብእና ሲይዙ በፈለጉት የሙያ ዘርፍ አሰልጥኖ ወደ ስራ ማስገባቱን ተናግረዋል። 

"ስልጠናና ድጋፍ ኢንቨስትመንት በመሆኑ ከፍተኛ ዋጋ አለው" ያሉት አቶ ሙሉጌታ ዋናው ጉዳይ ግን ተመራቂዎች ያገኙትን እውቀት፣ ክህሎትና ድጋፍ ተጠቅመው ሰርተው ሲለወጡ መሆኑን አስረድተዋል።

የአማራ ክልል ሴቶች፣ ህጻናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ምክትል ሃላፊ ወይዘሮ ሰላማዊት አለማየሁ በበኩላቸው ድርጅቱ ለብዙ ዘመናት የሴቶችን ህይወት ለመለወጥ በሚያደርገው ጥረት የሚታወቅ ነው።

በጣም በርካታ ቁጥር ያላቸው ተጋላጭ ሴቶችን ከአስከፊ ህይወት እንዲወጡ ባደረገው አስተዋጽኦ ሁላችንም የምንመሰክርለት ጉዳይ ነው ብለዋል።

"ለኢየሩሳሌም የህጻናትና ማህበረሰብ ልማት ድርጅት ውለታ ከፋዮች እኛ ተመራቂዎች ነን" ያሉት ወይዘሮ ሰላማዊት ተመራዊዎች በሚሰማሩበት የሙያ መስክ ሁሉ ውጤታማ በመሆን የድርጅቱን ስም ማስጠራት አለባቸው።

እስከ አሁን በነበረው ተሞክሮ ቁጥራቸው ምንም እንኳ ትንሽ ቢሆንም የሰለጠኑበትን ሙያና የተደረገላቸውን የስራ መነሻ ገንዘብና የመስሪያ ቁሳቁስ በማጥፋት ወደ ነበሩበት አስከፊ ህይወት የሚመለሱ እንደነበሩ አውስተዋል።

"አሁን ከነበራችሁበት አስከፊ የኑሩ ሁኔታ በመውጣት ያገኛችሁት እድል ቀላል አይደለም" ያሉት ወይዘሮ ሰላማዊት አሁን ባለንበት ዘመን ይህ እድል ዳግም የማትገኝ በመሆኑ ውጤታማ እንዲሆኑ አሳስበዋል።

በድርጅቱ የምክር አገልግሎት፣ የህይወት ክህሎት፣ የስነ ተዋልዶና የቁጠባ ስለጠናዎችን ከሙያ ስልጠናው አስቀድሞ እንድናገኝ አድርጓል ያለችው ደግሞ ከተመራቂዎች መካከል ወጣት ሰላማዊት ደሴ ናት።

ሰርተን ለመለወጥ የሚያስችለንን አስተሳሰብና አመለካከት ከያዝን በኋላ ደግሞ የምግብ፣ የመኖሪያና ለኑሯችን አስፈላጊ የሆኑ ቁሳቁሶችን አሟልቶ በምንፈልገው ሙያ ለ3 ወራት ስልጠና እንድናገኝ አድርጎናል ብላለች።

እሷም በሴቶች ጸጉር ሙያ ሰልጥና በ1ሺህ 500 ብር የተቀጠረች ሲሆን ድርጅቱ ደግሞ እስከምትቋቋም ለ6 ወራት ከድርጅቱ የሚሰጣትን 1500 ብር በመቆጠብ ላውንደሪ ለመግዛት አስባ እየሰራች መሆኑን ተናግራለች።

ሌላዋ ተመራቂ ኤልሳ አበበ እንዳለችው ድርጅቱ ከነበረችበት ችግር በማውጣት በወንዶች ጸጉር ቤት በማሰልጠን የሙያ ባለቤት ከማድረጉም በላይ እንዴት ሰርቶ መኖር እንደሚቻል አስተምሮኛል ብላለች።

አሁን ላይ በተሰጣት ስልጠና ተጠቅማ የተግባር ልምምድ እያደረገች በመሆኑ በቀጣይ ተቀጥራም ሆነ በግሏ በመክፈት ሰርታ ለመለወጥ ቁርጠኛ መሆኗን ተናግራለች።

ለፕሮጀክት ማስፈጸሚያ 60 ሚሊየን ብር የሚጠጋ ገንዘብ የስዊድን አለም አቀፍ ድርጅት በቀዳማዊት እመቤት ቢሮ በኩል በሚያደርገው ድጋፍ የሚንቀሳቀስ መሆኑ ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም