እየተደረገልን ያለው ድጋፍ ያጋጠመንን የከፋ ችግር ለመቋቋም እያገዘን ነው

97

ባህርዳር መስከረም 30/2014 (ኢዜአ) የአካባቢው ህዝብ፣ መንግስትና ግብረ ሰናይ ድርጅቶች በሚያደርጉት ድጋፍ ለከፋ ችግር አለመዳረጋቸውን ከዋግህምራ ዞን ተፈናቅለው በእብናት መጠለያ ጣቢያ የሚገኙ ወገኖች ገለጹ።

በአዲስ አበባ የሚኖሩ በጎ ፈቃደኞች "ለወገን እንድረስ" በሚል መሪ ሀሳብ ከ800 ሺህ ብር በላይ ግምት ያለው አልባሳትና የንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁስ በእብናት መጠለያ ጣቢያ ለሚገኙ ተፈናቃዮች ድጋፍ አድርገዋል።

ከዋግ ኽምራ ዞን ሰቆጣ ከተማ የመጡት አቶ ሸጋው ገብረህይወት እንደገለጹት በአሸባሪው ህውሃት ታጣቂዎች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው ወደ እብናት ከተማ ከመጡ አንድ ወር ሆኗቸዋል።

ወደ መጠለያው እንደገቡ በነፍስ ወከፍ 14 ኪሎ ግራም የዳቦ ዱቄት፣ ፍራሽና ብርድ ልብስ ድጋፍ በማግኘት እየኖሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።

አሁንም መጭው ጊዜ ከፍተኛ ውርጭ የሚከሰትበት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በልብስ እጦት እንዳይሰቃዩ ሰግተው እንደነበር ጠቁመው የተደረገላቸው የሙሉ ቱታ ድጋፍ  እንዳስደሰታቸው ተናግረዋል።

ሌላኛው ተፈናቃይ አቶ ፈቃዱ ፀጋየ በበኩላቸው "ከገባን ጀምሮ መንግስትና የተለያዩ ድርጅቶች ከሚያደርጉት ድጋፍ በተጨማሪ የእብናት ህዝብ ያልተቋረጠ ድጋፍ ለከፋ ችግር እንዳንጋለጥ አድርጎናል" ብለዋል።

"ቤትና ቀየን ለቆ በእርዳታ እንደመኖር አስከፊ ነገር የለም" ያሉት ተፈናቃዮቹ መንግስት አሸባሪውን ቡድን ከአካባቢያቸው በማስወጣት ወደ ቀያቸው ተመልሰው ሰርተው የሚኖሩበት ሁኔ እንዲመቻችላቸው ጠይቀዋል።

በአዲስ አበባ የሚኖሩ የኢትዮጵያ በጎ ፈቃድ አገልግሎት ቡድን አስተባባሪ ወይዘሮ ሀረጓ ማሞ በበኩላቸው አሸባሪው ቡድን በአማራና በአፋር ክልል የሚገኙ ዜጎችን ከቤት ንብረታቸው ማፈናቀሉን ተናግረዋል።

በዚህም በሀገር ውስጥና በውጭ የሚኖሩ  ኢትዮጵያዊያንና ሌሎች ተባባሪ  አካላትን  በማስተባበር "ለወገን እንድረስ" በሚል መሪ ሃሳብ ተፈናቃዮችን ለመደገፍ የሚያስችል ከ1 ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ብር በላይ ማሰባሰብ ተችሏል ብለዋል።

ከተሰበሰበው ገንዘብ ውስጥም ከ807 ሺህ ብር በላይ ወጭ 5ሺህ 778 ሙሉ ቱታና 7 ሺህ 618 የሴቶች የንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁስ በመጠለያው ለሚገኙ ተፈናቃዮች ድጋፍ አድርገዋል።

በቀሪው ገንዘብ ደግሞ በአፋር ክልል ለተፈናቀሉ ወገኖች ተመሳሳይ ድጋፍ እንደሚደረግ ጠቁመው  የተጀመረውን የሰብአዊነት መልካም ስራ ለማስቀጠልም መላ ህብረተሰቡ ድጋፍ እንዲያደርጉላቸው ጥሪ አቅርበዋል።

የዋግኽምራ ዞን የፀጥታ ጉዳዮች አማካሪና የእብናት መጠለያ ጣቢያ የሎጀስቲክስ አስተባባሪ አቶ ፈንታው ፈጠነ እርዳታውን በተረከቡበት ወቅት እንዳሉት ከዋግ ኽምራ የተፈናቀሉ ከ18 ሺህ 800 በላይ ሰዎች በመጠለያው ይገኛሉ።

"የእብናት ከተማ ህዝብ፣ መንግስትና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና በጎፈቃደኛ ሰዎች እያደረጉት ያለው ያልተቆጠበ ድጋፍ የሚበረታታ ነው" ብለዋል።

በተቋቋመው የሎጀስቲክስ ኮሚቴ አማካኝነት የሚመጣውን ድጋፍ በፍትሃዊነትና በግልጸኝነት ለተፈናቀሉ ወገኖቻችን ለማድረስ ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ አስረድተዋል።   

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም