በመተከል ዞን በነበረው የጸጥታ ችግር የወደሙ ትምህርት ቤቶች ጥገና ሊካሄድ ነው

60

አሶሳ፣  መስከረም 29 /2014 (ኢዜአ.) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን በነበረው የጸጥታ ችግር ምክንያት የወደሙ ትምህርት ቤቶች መልሶ ግንባታና ጥገና በቅርቡ እንደሚጀመር የክልሉ ትምህርት ቢሮ አስታወቀ፡፡

የቢሮው ምክትል ሃላፊ አቶ ዑመር መሐመድ ለኢዜአ እንዳሉት፤ በመተከል ዞን የጸጥታ ችግር ከ190 በላይ ትምህርት ቤቶች ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡

ለትምህርት ቤቶቹ ግንባታና ጥገናው 15 ሚሊዮን ብር መመደቡን  ገልጸዋል፡፡

ስራው በፍጥነት ተጠናቆ ትምህርት ቤቶቹ በአጭር ጊዜ አገልግሎት እንዲጀምሩ ቢሮው በትኩረት እየሠራ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

በተለይ ሙሉ በሙሉ ለወደሙት ትምህርት ቤቶች አካባቢ ጊዜያዊ መጠለያዎች ለማዘጋጀት ቁሳቁስ ግዢና ተጓዳኝ ተግባራት እየተከናወኑ ነው ብለዋል፡፡

በክልሉ ትምህርት ቤቶች የ2014 ትምህርት በቀጣዩ ወር  ኮሮናን ለመከላከል የወጡ  መመሪያዎችን ባስጠበቀ መልኩ እንደሚጀመር ተናግረዋል፡፡

የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል የተዘጋጁ አዲስ የመማሪያ መጻህፍት በተመረጡ ትምህርት ቤቶች በሙከራ ደረጃ ሥራ ላይ እንደሚውሉ ሃላፊው ጠቁመዋል፡፡

የአሶሳ ካቶሊክ የመጀመሪያና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር ዘሪሁን ደሲሳ፤ ትምህርት ቤቱ የመማሪያ ክፍሎች ጥገናና የተማሪዎች ምዝገባ አጠናቋል ብለዋል፡፡

በክልሉ በተያዘው የትምህርት ዘመን ከ678 በላይ ትምህርት ቤቶች ከ302 ሺህ በላይ ተማሪዎች ትምህርታቸውን ይከታተላሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ከትምህርት ቢሮው የተገኘው መረጃ ያስረዳል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም