ሕይወትን ከማዳን ጋር የተቆራኘው የጤና መረጃ አያያዝ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል

110

አዲስ አበባ፤ መስከረም 29 ቀን 2014 (ኢዜአ) ሕይወትን ከማዳን ጋር የተቆራኘው የጤና መረጃ አያያዝ ያለውን ፋይዳ በመገንዘብ ተገቢውን ትኩረት መስጠት እንደሚገባ የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ ገለጹ።

የኢትዮጵያን የጤና መረጃ ስርዓት ማዘመን ዓላማ ያደረገው የአቅም ግንባታ ስልጠና መርሃ ግብር (ሲቢኤምፒ) አፈጻጸምና ቀጣይ አካሄድ በተመለከተ የተዘጋጀው አውደ ጥናት ዛሬ በአዲስ አበባ ተካሄዷል።

በ2011 ዓ.ም ይፋ የተደረገው መርሃ ግብር የጤና ሚኒስቴር ከዩኒቨርሲቲዎችና የክልል የጤና ቢሮዎች ጋር በመሆን በሁሉም ክልሎችና በሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች በሚገኙ 36 ወረዳዎች እየተተገበረ ይገኛል።

በዚህ መርሃ ግብር የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ዋነኛ ተዋናይ ሲሆኑ፤ የጤና መረጃ ስርዓቱን ለማዘመን አስተዋጽኦ ያደርጋሉ፤ ሳይንሳዊ መረጃን የማመንጨት ሃላፊነት ተጥሎባቸው እየሰሩ ይገኛሉ።

በዚሁ ወቅት የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ እንደገለጹት፤ መንግስት በጤና ፖሊሲና ስትራቴጂዎቹ ዋንኛ ትኩረት ከሰጣቸው ጉዳዮች አንዱ የጤና መረጃ ስርዓቱን ማዘመን ነው።

የጤና መረጃ አያያዝና አጠቃቀም ለጤና አገልግሎት ጥራት መሻሻልና ለጤና ስርዓቱ መጠናከር አስተዋጽኦ ያለው መሆኑን አመልክተው፤ ይህንኑ ፋይዳ በመረዳት የተለያዩ ስራዎች ሲከናወኑ መቆየታቸውን ተናግረዋል።

ከነዚህ ውስጥ የአቅም ግንባታና የስልጠና መርሃ ግብር አንዱ እንደሆነ ጠቅሰዋል።

መርሃ ግብሩን አስመልክቶ በተደረገ የመነሻ ጥናት በአገር አቀፍ ደረጃ በሁለት ዓመት የትግበራ ጊዜ ውስጥ 135 የጤና ተቋማት የጤና መረጃ የመሰብሰብና ለውሳኔ የመጠቀም ምጣኔያቸው ወደ 62 በመቶ ማደጉን አመልክተዋል፤ ይህም “የጤና መረጃ ስርዓቱ እየተሻሻለ መሆን ማሳያ ነው” ብለዋል።

ለጤና መረጃ አሰባሰብ ተገቢውን ትኩረት አለመስጠት በዚህም ለጤና ስርዓቱ የሚያስፈልጉ መረጃዎች በሚፈለገው መጠን እንዳይሰበሰቡ ምክንያት መሆኑን አብራርተዋል።

“የጤና መረጃ ሕይወትን የሚያድን ነው” ያሉት ዶክተር ሊያ፤ ሁሉም የጤና ዘርፍ ባለድርሻ አካላት ለጤና መረጃ አሰባሰብ ተገቢውን ትኩረት መስጠትና በጤና ስርዓት ውሰጥ ባህል እንዲሆን መስራት እንደሚጠበቅባቸው ተናግረዋል።

በቀጣይ መርሃ ግብሩን የሚተገብሩ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን የማሳደግና አድማሱን የማስፋት ስራ እንደሚከናወን ጠቁመዋል።

በጅማ ዩኒቨርሲቲ የአቅም ግንባታ ስልጠና መርሃ ግብር ዳይሬክተር ዶክተር ሙሉእመቤት አበራ እንደገለጹት፤ መርሃ ግብሩ ጥራት ያለው መረጃ አያያዝ ከማቅረብና መረጃውን ለውሳኔ ከመጠቀም አኳያ መሻሻሎች ታይተዋል።

ዩኒቨርሲቲው ስልጠናና ድጋፍ በሚሰጥባቸው በጋምቤላና ኦሮሚያ ክልሎች የሚገኙ የጤና ተቋማት ጥራት ያለው መረጃ የመሰብሰብ አቅማቸው ማደጉን ጠቁመው፤ መረጃ ለውሳኔ የመጠቀም ምጣኔው ወደ 64 በመቶ ከፍ ማለቱን በማሳያነት ጠቅሰዋል።

በተጨማሪም መርሃ ግብሩ ከጤና መረጃ አያያዝ ጋር ከፈጠረው መሻሻል ባለፈ የዩንቨርሲቲና የኢንዱስትሪው ትስስር ላይ ለውጥ ማምጣት የሚቻልባቸው ጅምር ውጤቶች ያስገኘ መሆኑን አመልክተዋል።

ይሁንና አሁንም የጤና መረጃ አያያዝና አጠቃቀም ባህል ማሳደግ እንደሚገባ ጠቁመው፤ ለጤና መረጃ የሚያስፈልጉ መሰረተ ልማቶች ማሟላት እንዳለባቸው ተናግረዋል።

የጤና መረጃ አያያዝ ቁልፍ የጤና ዘርፍ ስራ መሆኑን ጠቅሰው፤ መንግስት ለተግባራዊነቱ ያለውን ቁርጠኝነት ማሳደግ እንዳለበትም ዶክተር ሙሉእመቤት ተናግረዋል።

የአማራ ክልል የጤና ቢሮ የእቅድ ዝግጅት ዳይሬክተር አቶ ተክለሃይማኖት ገብረሕይወት በኩላቸው፤ “የጤና መረጃ አያያዝ ስርዓትን በተመለከተ ያሉ የአመለካከት ችግሮች መቃለል አለባቸው” ብለዋል።

“የጤና መረጃ ሰብሳቢን ሚናን አሳንሶ የማየትና አንድ በጤና ተቋም ውስጥ  የሚሰራን ግለሰብ ሲያጠፋ  መረጃ መሰብሰብ ክፍል ማስገባት እንደ ቅጣት ይወሰዳል” ሲሉ የገለጹት ዳይሬክተሩ፤ ይሄ በመረጃ አያያዝና አጠቃቀም ላይ ችግር የሚፈጥር በመሆኑን ሊስተካከል እንደሚገባ አመልክተዋል።

መርሃ ግብሩ የጤና መረጃ ከማሰባሰብ ባለፈ አድማሱን አስፍቶ በሌሎች የጤና ዘርፎችም ዩኒቨርስቲዎችና የጤና ቢሮዎች እንዲሰሩ መደረግ እንዳለበት ገልጸዋል።

የኢትዮጵያን የጤና መረጃ ስርዓት ማዘመን አላማ ያደረገው የአቅም ግንባታ ስልጠና መርሃ ግብር የመጀመሪያ ዙር ትግበራ በሰኔ 2014 ዓ.ም ይጠናቀቃል።

ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማትና የልማት አገሮች የተገኘ 80 ሚሊዮን ብር እስካሁን ላለው የመርሃ ግብሩ ማስፈጸሚያ ወጪ ተደርጓል።

የጤና ሚኒስቴር ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ እያደረገው ከሚገኘው የጤናው ዘርፍ ትራንስፎርሜሽን እቅድ አራት ምሰሶዎች አንዱ የጤና መረጃ ስርዓቱን በማዘመን የመረጃ አብዮት መፍጠር ነው።