ለኢትዮጵያ ልማትና ብልጽግና ሃላፊነታቸውን ለመወጣት ተዘጋጅተዋል

52

አዲስ አበባ፤ መስከረም 29 ቀን 2014 (ኢዜአ) በተመረቁበት የትምህርት መስክ በቅንነት በማገልገል ለአገራዊ ልማትና ብልጽግና የበኩላቸውን ኃላፊነት ለመወጣት መዘጋጀታቸውን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ምሩቃን ተናገሩ።

አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለ72ኛ ጊዜ በተለያዩ የትምህርት መስክ ያስተማራቸውን ከስድስት ሺህ በላይ ተማሪዎች በዛሬው ዕለት አስመርቋል።

ዮኒቨርሲቲው በወዳጅነት አደባባይ በቅድመ እና ድህረ ምረቃ ያስመረቃቸው ተማሪዎች በመደበኛ፣ በማታ እና በርቀት ትምህርት መርኃ-ግብር ትምህርታቸውን ሲከታተሉ የቆዩ ናቸው።

በስነ-ስርዓቱ ላይ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ፣ የትምህርት ሚኒስትሩ ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር)፣ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች፣ የተማሪ ቤተሰቦችና ተጋባዥ እንግዶች ታድመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ያነጋገራቸው ተመራቂዎች እንደገለጹት፤ በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ያካበቱትን እውቀትና ክህሎት ለበጎ ዓላማ በማዋል በቅንነትና ታማኝነት ህዝብንና አገርን ለማገልገል ይተጋሉ።

ዶክተር ዮሴፍ ሃላላ እንደሚናገሩት፤ ከዩኒቨርሲቲ መምህርነት በተጨማሪ የኢትዮጵያ እድገት የሚያሳልጡ የጥናትና ምርምር ስራዎችን በማካሄድ የበኩላቸውን ይወጣሉ።

በየካቲት-12 ሜዲካል ኮሌጅ የህክምና መምህሩና የማክሮ ባይዎሎጂ ምሩቁ አየልኝ ደርቤ በበኩሉ፤ ምርቃት ደስታን ከመቸሩ ባለፈ ለአገርና ህብረተሰብ ለውጥ ተጨማሪ ኃላፊነትን የሚሰጥ መሆኑን ተናግሯል።

ምርቃቱም ኃላፊነትን ለመወጣት ቃል-ኪዳን የሚገባበትና ለበለጠ አገራዊ ለውጥ ድርብ ኃላፊነትን የሚሰጥ ክስተት መሆኑን ገልጿል።

በተሰማራበት የሙያ መስክ ለተሻለ አገራዊ ስኬት እንደሚተጋ ጠቁሞ፤ ተመራቂዎችም ቀጣይ በሚሰማሩበት ሙያ ሁሉ ውጤታማ ተግባራትን ማከናወን እንደሚጠበቅባቸው ተናግሯል።

የማኔጅመንት የትምህርት ክፍል ምሩቃኑ ምሩጽ ተወልደ እና ቃል-ዓብ ኃይሌ እንደሚሉት፤ በተማሩበት ሙያ ስራ ፈጣሪ በመሆን ለቤተሰብና አገር ልማት መትጋት ያስፈልጋል።

"አገር ሲኖር ነው መማርም ሆነ ውሎ መግባት የሚቻለውና ሁሉም ኢትዮጵያዊ ቅድሚያ ለአገሩ ዘብ በመሆን የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ማስቀጠል ይገባል" ብለዋል አስተያየት ሰጪዎቹ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም