መንግስት ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ተቀራርቦ መስራት መጀመሩ ሁለንተናዊ ለውጥ ለማምጣት ትልቅ አስተዋጽኦ አለው

103

አዲስ አበባ፣ መስከረም 29/2014(ኢዜአ) መንግስት ከተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ከሌሎች አካላት ጋር ተቀራርቦ መስራት መጀመሩ ሁለንተናዊ ለውጥ ለማምጣት ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት የእናት ፓርቲ አስታወቀ።

የብልጽግና ፓርቲ በሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም በተካሔደው ምርጫ አብላጫ ድምጽ አግኝቶ ቢያሸንፍም የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ አባላትን በተለያዩ የሥራ ሃላፊነት ቦታ ላይ በመመደብ ተቀራርቦ ለመስራት እያደረገ ያለው ጥረት እንደሚደነቅ ብዙዎች እየተናገሩ ናቸው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አሕመድ በቅርቡ ባዋቀሩት የሚኒስትሮች ምክር ቤት ውስጥ ሶስት የተፎካካሪ ፓርቲ አባላትን አካተዋል።

ዛሬ ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የወጣው ሹመትን የተመለከተው መረጃ፤ ከተሿሚዎቹ መካከል የተፎካካሪ ፓርቲ አመራር አካላት የተካተቱ ከእናት ፓርቲ ወይዘሮ ጥሩማር አባተ የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዴኤታ እንዲሁም ከነጻነትና እኩልነት ፓርቲ ወይዘሮ ነብያ መሃመድ የስራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሆነው ተሹመዋል፡፡

የእናት ፓርት ሊቀ መንበር ዶክተር ሰይፈሥላሴ አያሌው ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንደገለጹት፤ መንግስት በአገር ደረጃ ተቀራርቦ ለመስራትና ለመደማመጥ የጀመራቸው ተግባራት ሁለንተናዊ ለውጥ ለማምጣት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ።

በአሁኑ ወቅት መንግስት እያከናወናቸው ያሉት ተግባራት ''በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ ታይተው የማይታወቁ በልማዳዊ አካሔድ ሲተገበሩ ከነበሩት የተለዩ ናቸው" ብለዋል።

ይህ አካሔድ ደግሞ በአገር ጉዳይ ላይ ሁሉም ተባብሮ እንዲሰራና አካታችነት እንዲመጣ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ መሆኑን እንደሚያሳይ ተናግረዋል።

"የእናት ፓርቲ መንግስት ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር ተቀራርቦ ለመስራት ባቀረበው ጥያቄ ላይ በስራ አስፈፃሚና በላዕላይ ምክር ቤት ደረጃ በጥልቀት ተወያይቶበታል፤ አካሔዱም በጎ ጅማሬ መሆኑ ስምምነት ላይ ደርሷል'' ብለዋል።

በአገር ጉዳይ ተቀራርቦና ተደማምጦ በጋራ መስራት ከድህነት ለመውጣት በሚደረገው ጥረት ውስጥ የጎላ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ጠቁመው፤ የፖለቲካ ምሕዳሩን በማስፋት ረገድ አዎንታዊ ሚናው ከፍተኛ እንደሆነም ጠቁመዋል።

ከዚህ ቀደም የአገሪቷ የፖለቲካ አካሔድ የአውራ ፓርቲ ፈላጭ ቆራጭነት ብቻ እንደነበር አስታውሰው፤ የዚህ ዓይነቱ አካሔድ ለኢትዮጵያ የሚጠቅም እንዳልሆነ በተጨባጭ መታየቱን አውስተዋል።

በመሆኑም ለተፎካካሪ ፓርቲዎች የተሰጠው የመንግስት ሹመት የስራ ቦታ ብቻ ሳይሆን አሳታፊነቱንም የሚያሳይ በመሆኑ እንደሚደነቅ ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት በመንግስት ሹመት ያገኙት ሁሉም ዜጎች "በሙያቸው አገርን ለማገልገል የተሰጣቸውን ኃላፊነት በአግባቡ ሊወጡ ይገባል" ሲሉም አሳስበዋል።

ይህ ሹመት በአስፈፃሚ አካላት ዘንድም በተለያዩ ጉዳች ላይ ለየት ያለ ድምጽ እንዲሰማ፣ ሐሳቦች ተነስተው እንዲሸራሸሩ እድል እንደሚሰጥም ነው የተናገሩት ።

ተሿሚዎች የተሰጣቸውን ኃላፊነት በብቃት በመወጣት እንደ አገር ከአገር ውስጥና ከውጭ እየገጠመ ያለውን ጫና ለመቋቋም ዋነኛ ተዋናኝ ሊሆኑ እንደሚገባም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም