ተመራቂዎች በቆይታቸው ያካበቱትን እውቀት ለአገራቸው እድገትና ብልፅግና ማዋል ይጠበቅባቸዋል

93

አዲስ አበባ፣ መስከረም 29/2014(ኢዜአ) ተመራቂ ተማሪዎች በትምህርት ቆይታችሁ ያካበታችሁትን እውቀት ለአገራችሁ እድገትና ብልፅግና ማዋል ይጠበቅባችኋል ሲሉ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና ተናገሩ።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያሰለጠናቸው ተማሪዎች አስመርቋል።

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና ፤ "ተመራቂዎች የአመታት የልፋት ውጤታችሁን ለምታዩበት የተለየ ቀን በመድረሳችሁ እንኳን ደስ ያላችሁ ብለዋል።

ኢትዮጵያ በተለያዩ ፈተናዎች ውስጥ አልፋ የነገን ብሩህ ተስፋ ለማየት በርካታ አገራዊ ጉዳዮች በከወነችበት ማግስት በመመረቃችሁም የተለየ አጋጣሚ ነው ሲሉ ጠቅሰዋል።

በመሆኑም ተመራቂ ተማሪዎች በትምህርት ቆይታችሁ ያካበታችሁትን እውቀት ለአገራችሁ እድገትና ብልፅግና ማዋል ይጠበቅባችኋል ሲሉ አሳስበዋል።

አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለበርካታ አመታት የቆየው የሂሳብ ኦዲት በተጠናቀቀበት እና ዩኒቨርሲቲውን የምርምር ተቋም በማድረግ በአፍሪካና ዓለም አቀፍ ደረጃ የላቀ አፈፃፀም ማስመዝገቡን ተናግረዋል።

ዩኒቨርሲቲው በዓለም አቀፍ ደረጃ ተጽዕኖ ፈጣሪ የሆኑ መጽሄቶችና ሳይንሳዊ የምርምር አርቲክሎች በማሳተም ኢትዮጵያንና አፍሪካን ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ እያስተዋወቀ እንደሚገኝ አመላክተዋል።

ዩኒቨርሲቲው ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ስኬት የሚጠበቅበትን የምርምር፣ የገንዘብ ድጋፍ እና የዲፕሎማሲ ስራ እያከናወነ እንደሚገኝም ገልጸዋል።

በህግ ማስከበር ዘመቻው የገንዘብ፣ የህክምና እና ሌሎች ሰብዓዊ ድጋፍ ማድረጉን አስታውሰው የዛሬ ተመራቂዎች ከመንግስት ጎን በመሰለፍ ኢትዮጵያን ከውስጥና ከውጭ ጠላቶች መጠበቅ አለባቸው ብለዋል።

አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለ72ኛ ጊዜ በመደበኛ፣ በማታና በርቀት የትምህርት መርሐግብሮች ያስተማራቸውን 6 ሺህ 163 በቅድመና ድሕረ ምረቃ ተማሪዎች በወዳጅነት አደባባይ አስመርቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም