ጤና ሚኒስቴር፣ የመድሃኒት አቅርቦት ኤጄንሲና ፅናት ለኢትዮጵያ ቡድን ለመከላከያ ሠራዊት ድጋፍ አደረጉ

መስከረም 28/2014(ኢዜአ) ጤና ሚኒስቴር፣ የመድሃኒት አቅርቦት ኤጄንሲ እና ፅናት ለኢትዮጵያ ቡድን ለመከላከያ ሠራዊት የአይነትና የገንዘብ ድጋፍ አበርክተዋል።

 ድጋፉን የተረከቡት የመከላከያ ሠራዊት የድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴ ሰብሳቢ ብርጋዴር ጄኔራል አስረስ አያሌው ሲሆኑ የመድሃኒት አቅርቦት ኤጀንሲ የ10 ሚሊዮን ብር የገንዘብ ድጋፍ አድርጓል።

ገንዘቡ የተቋሙ ሠራተኞች የአንድ ወር ደመወዛቸውን ለመስጠት ቃል በገቡት መሰረት የተሰበሰበ መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ አቶ አብዱ ገልጋሎ ተናግረዋል።

የጤና ሚኒስቴር የሕክምና ባለሙያዎችን ግንባር ድረስ ከመላክ ጀምሮ ከጤና ጋር የተያያዙ እገዛዎችን ሲያደርግ መቆየቱን የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ አለምፀሃይ ጳውሎስ ተናግረዋል።

ሚኒስትር ዴኤታዋ የመድሃኒት አቅርቦት ኤጀንሲ ያበረከተውንና በሚኒስቴሩ ሠራተኞች የተዘጋጀ ደረቅ ምግብ አስረክበዋል።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ሲያደርጋቸው የነበሩ ሁለንተናዊ ድጋፎችን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልፀዋል።

በዓለም ላይ ያሉ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ለአገራቸው ድጋፍ ለማድረግ የተመሰረተው ፅናት ለኢትዮጵያ ቡድን ደግሞ 125 ሺህ ብር የሚገመት የሴቶች ንፅህና መጠበቂያና የተለያዩ አልባሳት ሰጥቷል።

ድጋፉን ያስረከቡት የቡድኑ አባል አቶ ፋሲል አጥሌ በአገር ውስጥና ከአገር ውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን የአገራቸውን ህልውና ለመጠበቅ አንድ መሆን እንዳለባቸውና ድጋፋቸውን እንዲያጠናክሩ ጥሪ አቅርበዋል።

የመከላከያ ሠራዊት የድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴ ሰብሳቢ ብርጋዴር ጄኔራል አስረስ አያሌው ኢትዮጵያዊያን አገራቸውን ለማዳን በንቃት መሳተፍ እንዳለባቸው ተናግረዋል።

ለሠራዊቱ ለተደረገው ድጋፍም ምስጋና አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም