ለስኳር ህሙማን ኢንሱሊን በተመጣጣኝ ዋጋ ተደራሽ ማድረግ የሚያስችል ፕሮጀክት ይፋ ተደረገ

82

አዲስ አበባ መስከረም 28/2014 (ኢዜአ)  ለስኳር ህሙማን ኢንሱሊን በተመጣጣኝ ዋጋ ተደራሽ ማድረግ የሚያስችል "አይ ኬር" የተሰኘ ፕሮጀክት ይፋ ተደረገ።

 ፕሮጀክቱን ይፋ ያደረጉት የስኳር ህሙማን ማህበር፣ የጤና ሚንስቴር ፣ የኢትዮጵያ መድሃኒት አቅራቢ ኤጀንሲ እና  'ኖቮ ኖርዲስክ' የተባለ የዴንማርክ መድሃኒት አቅራቢ ድርጅት በጋራ በመሆን ነው፡፡

ፕሮጀክቱ በቀጣይ ሶስት ዓመታት በስኳር ህሙማን የመድሃኒት አቅርቦት ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሰራ ነው ተብሏል።

የፕሮጀክቱ ዋነኛ ዓላማ በኢትዮጵያ ያሉ የስኳር ህሙማን ኢንሱሊን የተባለውን መድሃኒት በተመጣጣኝ እና አነስተኛ ዋጋ እንዲያገኙ ማስቻል ነው ተብሏል።

የስኳርና ሆርሞን ህክምና ስፔሻሊስት እና የኢትዮጵያ ስኳር ህሙማን ማህበር ፕሬዝዳንት ዶክተር ጌታሁን ታረቀኝ እንዳሉት በዓለም አቀፍ ደረጃ የስኳር ህሙማን ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መጥቷል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ 460 ሚሊዮን ሰዎች ከስኳር ህመም ጋር እንደሚኖሩ ገልጸው፤ ከዚህም ውስጥ 19 ሚሊዮኑ በአፍሪካ ይገኛሉ ነው ያሉት።

ከኮቪድ 19 ወረርሽኝ ጋር ተያይዞ  የስኳር ህመም በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ እንደሚገኝም ጠቁመዋል። 

ማህበሩ እድሜያቸው ከ23 ዓመት በታች ለሆኑ የስኳር ህሙማን ያለምንም  ክፍያ መድሃኒቱን እየሰጠ እንደሚገኝ ጠቅሰው፤ በፕሮጀክቱ አማካኝነት ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውና ህክምናውን በቅርበት ለማያገኙ ዜጎች ኢንሱሊን በዝቅተኛ ዋጋ ተደራሽ እደሚሆን ተናግረዋል፡፡

በጤና ሚኒስቴር የበሽታዎች መከላከልና መቆጣጠር ዳይሬክተር ወይዘሮ ህይወት ሰለሞን በበኩላቸው ፕሮጀክቱ ከኢንሱሊን አቅርቦት በተጨማሪ የመመርመሪያ መሳሪያዎች አቅርቦት እና የስኳር ህመም ግንዛቤ ማሳደግ ስራ ማካተቱን ገልጸዋል።

ሚንስቴሩ በጤናው ዘርፈ ያለውን ተላላፊ እና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን በተቀናጀ መልኩ የሚመራበት ፖሊሲ ቀርጾ እየሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ኢንሱሊን ወደ ሀገር ውስጥ በበቂ ሁኔታ እንዲገባ በመንግስት በኩል አስፈላጊው ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰው፤ ፕሮጀክቱ የኢንሱሊን አቅርቦትን በማሻሻል ረገድ ሚናው የጎላ መሆኑን  አስረድተዋል።

ኢትዮጵያ የጤና ተደራሽነትና ጥራት ለማሻሻል የምታደርገውን ጥረት የዴንማርክ መንግስት እንደሚደግፈው የተናገሩት ደግሞ በኢትዮጵያ የዴንማርክ አምባሳደር ኪራ ስሚዝ ናቸው፡፡

ፕሮጀክቱ የኢንሱሊን አቅርቦትን በማሳደግ በስኳር ህመም ሳቢያ የሚደርሰውን ከፍተኛ ጉዳት በመቀነስ ረገድ የማይተካ ሚና አለው ብለዋል።

በኢትዮጵያ 1.7 ሚሊዮን ሰዎች ከስኳር ህመም ጋር እንደሚኖሩ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም