ደቡብ ኮርያ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን አጋርነት ታጠናክራለች

88

አዲስ አበባ መስከረም 28/2014 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ ሠላምና ብልጽግናን ለማረጋገጥ የምታደርገው ጥረት እንዲሳካ ደቡብ ኮርያ አጋርነቷን አጠናክራ እንደምትቀጥል በኢትዮጵያ የአገሪቱ አምባሳደር ካንግ ሲዮክ ሂ ገለጹ።

በሕዝብ ለተመረጠው አዲሱ የመንግሥት ምሥረታ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክትም አስተላልፈዋል።

አምባሳደር ካንግ ሲዮክ ሂ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ አገራቸው በኢትዮጵያ ሠላምና ብልጽግና እንዲረጋገጥ የምታደርገውን ድጋፍ ታጠናክራለች ብለዋል።

ሁለቱ አገራት ጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንዳላቸውና በተለይም ኢትዮጵያ ለኮርያ ልዩ አገር መሆኗን አንስተው አጋርነቷን እንደምታጠናክር ነው የገለጹት።

ለሠላምና ልማት መረጋገጥ ብዙ ርቀት መጓዝ እንደሚያስፈልግ ጠቁመው ኢትዮጵያ ኮርያን ጨምሮ ከዓለም አገራት ጋር ያላት አጋርነት ለስኬት ያበቃታል ብለዋል።

ኮርያ በማደግ ላይ ከነበሩ አገራት ወጥታ ወደ አደጉ አገራት ተርታ የተሰለፈች መሆኗን ጠቁመው ይህንን ልምዷን ለኢትዮጵያ እያካፈለች መሆኗን አክለዋል።

ኮርያ በኢትዮጵያ የምታካሂደው የልማት ፕሮጀክት በሌሎች የአፍሪካ አገራት ከምታካሂዳቸው መካከል ትልቁ መሆኑን አንስተዋል።

እነዚህም ፕሮጀክቶች በጤና፣ በግብርና፣ በትምህርትና በሌሎች የመሰረተ ልማት ግንባታ ሥራዎች ላይ ትኩረት ማድረጋቸውን ገልጸው የዘርፎቹም አጋርነት ይጠናከራል ነው ያሉት።   

በተመሳሳይ በንግድና ኢንቨስትመንት ዘርፍ በተለይም ደግሞ የሁለቱን አገራት የግሉን ዘርፍ ግንኙነት  ለማጠናከርም ይሰራል ብለዋል።  

በኢትዮጵያ 20 የኮርያ ኩባንዎች መኖራቸውን የጠቀሱት አምባሳደሩ የኢትዮጵያን የኢንቨስትመንት አማራጮች በማስተዋወቅ ቁጥሩ ከፍ እንዲል እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።

ከዚህ ባለፈ በዓለም አቀፍ ጉዳዮች፤ በአየር ንብረትና በሠላም ማስከበር ላይ ኮርያ ከኢትዮጵያ ጋር ተባብራ የምትሰራውን ሥራ ለማጠናከር እንደሚሰሩም ተናግረዋል።

ኢትዮጵያና ደቡብ ኮርያ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን የጀመሩት እንደ አውሮፓዊያኑ አቆጣጠር በ1960ዎቹ መጀመሪያ ላይ መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም