መንግስት የሰብዓዊ መብት ጥሰት በሚፈፅሙ አካላት ላይ ተገቢውን እርምጃ እንዲወድስ ተጠየቀ

74
አዲስ አበባ ነሀሴ 11/2010 በኢትዮጵያ አንዳንድ አካባቢዎች ከሚስተዋሉ የሁከት ተግባራት ጋር ተያይዞ የሚፈፀሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ለመከላከል መንግሥት ጥፋት በሚፈጽሙ አካላት ላይ እርምጃ እንዲወስድ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ጠየቁ። በአንዳንድ የአገሪቱ ክፍሎች እየተፈጠሩ ባሉ ሁከቶች ሳቢያ የሰው ህይወትና ንብረት እየጠፋ ከመሆኑም በላይ አያሌዎች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው እርዳታ ጠባቂ ሆነዋል። መንግስት በመላው ዜጋ መካከል በፍቅርና መተሳሰብ ላይ የተመሰረተ አንድነትን ለመገንባት፣ የአገሪቱን የወጪ ንግድ ለማጠናከርና የዜጎችን  የስራ አጥነት ችግር ለመቀነስ የሚያስችሉ እርምጃዎችን እየወሰደ ነው። ሆኖም ከየአካባቢው የሚሰማው የጥፋት ተግባር የዜጎችን ደህንነትና የፖለቲካ ኢኮኖሚ ተጠቃሚነት አደጋ ላይ እንዲወድቅ ከማድረግ ባለፈ የአገሪቱን የወደፊት ተስፋ የሚያጨልም አደገኛ ክስተት በመሆኑ ከወዲሁ ሊገታ እንደሚገባው ነው አስተያየት ሰጪዎቹ የተናገሩት። በመሆኑም መንግሥት እንዲህ ያሉ ተግባራትን በመፈጸም የህብረተሰቡን ሰላም የሚያውኩ ግለሰቦችን ተጠያቂ ማድረግ እንዳለበት ተናግረዋል። ይህንንም ተከትሎ ሌሎች አካላት ተመሳሳይ ጥፋት እንዳይፈጽሙ ለማስቻል በጥፋተኞቹ ላይ አስተማሪ እርምጃ እንዲወስድ ጠቁመዋል። ህብረተሰቡም የተጀመረውን የለውጥ ጉዞ ለማደናቀፍ የሚጥሩ አካላትን በማጋለጥ ግንባር ቀደም በመሆን ኃላፊነቱን በአግባቡ መወጣት እንዳለበትም አሳስበዋል። የዜጎችን ሰብዓዊ መብት ለማስከበርና ጥፋተኞችን በህግ አግባብ መሰረት በፍርድ ቤት ቀርበው ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኙ ማድረግ እንደሚገባም አስገንዝበዋል። የከተማዋ ነዋሪ ከሆኑት ግለሰቦች መካከል አቶ ኢርኮ ኡርጋ በተለይ በሻሸመኔ የተደረገው ነገር በጣም አስከፊና አሰቃቂ የሆነ ነገር መሆኑን ጠቁመው ይህን ተግባር የፈፀመ ማንኛውም አካል ወደ ህግ መቅረብ አለበት ብለዋል፡፡ ሌላው ነዋሪ አቶ ሰለሞን ገብረሲሳይ በበኩላቸው ሰብአዊ መብት ማለት አንድ ሰው በነጻነት የመዘዋወርና የመስራት መብት ሲኖረውና ለዚህም የህግ ጥበቃ  እና ከለላ ሲኖረው ነው፡፡ በተረፈ ይህን መሰል ከህግ ውጭ የሆነ ነገር የሚፈጽሙ አካላት ላይ እርምጃ በመውሰድ ለሌሎች ትምህርት መስጠት ይገባል ብለዋል፡፡ ነዋሪዎቹም ከመንግሥት ጎን በመቆም የአከባቢያቸውን ሰላምና ደኅንነት ለመጠበቅ የድርሻቸውን ለመወጣት ቃል ገብተዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም