መንግስት አሳታፊ ስርዓት ለመፍጠር የገባውን ቃል በተግባር ማሳየት ጀምሯል

56

ሀዋሳ፤ መስከረም 28/2014 (ኢዜአ) ባለፉት ሶስት ዓመታት መንግስት አሳታፊ ስርዓት ለመፍጠር የገባውን ቃል በተግባር ማሳየት መጀመሩ በህብረተሰቡ ዘንድ እምነት እንዲያሳድር የሚያደርግ መሆኑን አስተያየት ሰጪዎች ተናገሩ።

ከደቡብ ክልል  አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ነዋሪዎች እንዳሉት፤መንግስት አሳታፊ ስርዓት ለመፍጠር እንደሚሰራ ሲገልጽ የነበረውን በአዲሱ የካቢኔ ሹመት የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችን ማካተቱ ቃል የገባውን ወደ ተግባር መቀየር ስለመጀመሩ ማሳያ ነው።

 ይህም የዴሞክራሲ ምህዳርን ለማስፋት መሰረት የሚጥል በመሆኑ በቀጣይ ተጠናክሮ መሄድ ያለበት ነው።

የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ሰራተኛ አቶ ሃይሌ በይ ፤ የተለያዩ የፖለቲካ እይታ ያላቸውን ግለሰቦች በካቢኔ ሹመት ተካተው ማየት በመቻላቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል።

አዲሱ ጅማሮ የሃሳብ ብዝሃነት የሚስተናገድበትና እውነተኛ ዴሞክራሲን ለማበልጸግ መደላድል እንደሚሆን  ጠቁመዋል።

''ይህ ለኢትዮጵያ አዲስ ትንሳኤ ነው'' ያሉት አቶ ሃይሌ፤ ክስተቱ ሁሉም ዜጋ በሀገር ጉዳይ እኩል ባለቤት ሆኖ የሀገር ህልውና ለመጠበቅና  አንድነትን እንደሚያጠናከር ነው የተናገሩት።

አዲስ የተሾሙ ሚኒስትሮች ህዝቡን በማስተባበር የሀገርን ሰላምና የዜጎችን ደህንነት ማስጠበቅ የቅድሚያ ቅድሚያ ተግባራቸው ሊሆን እንደሚገባ አመልክተዋል።

ባለፉት 27 ዓመታት የተዘራውን የልዩነትና የዘረኝነት ትርክት በመንቀል የሀገራዊ አንድነት እሳቤ ጎልብቶ እንዲወጣ ማስቻልም የአዲሱ ካቢኔ ስራ መሆን እንዳለበት ጠቁመዋል።

በክልሉ የሃዲያ ዞን ነዋሪ   አቶ ታምራት ላምቤቦ፤  ባለፉት ሶስት ዓመታት መንግስት አሳታፊ ስርዓት ለመፍጠር የገባውን ቃል በተግባር ማሳየት መጀመሩ በህብረተሰቡ እምነት እንዲያሳድር የሚያደርግ መሆኑን ተናግረዋል።

በአዲሱ የካቢኔ ሹመት የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ አመረሮችን መካተት መቻሉ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ሀገር ለመቀየር በጋራ እንዲሰራ የሚያነሳሳ መሆኑን ጠቁመዋል።

''አሁን ላይ አሳታፊ መንግስት ተዋቅሯል። በምርጫ እንዲመራን እድል የሰጠነው መንግስት ስኬታማ እንዲሆን ሁሉም ዜጋ ካለልዩነት በተሰማራንበት መስክ ውጤታማ መሆን አለብን'' ብለዋል።

የካቢኔው ሹመት የተለያየ የፖለቲካ አስተሳሰብ ያላቸው ተወካዮች በሀገር ጉዳይ ላይ አንድ ሆነው እንዲሰሩ መሰረት መጣሉ የገለጹት ደግሞ የክልሉ  ምክር ቤት ሰራተኛ አቶ አሻግሬ አሰፋ ናቸው።

አቶ አሻግሬ እንዳሉት፤ በፖለቲካው ዘርፍ መታየት የጀመረው አዲስ የሽግግር ምዕራፍ እውቀትን፣ ልምድና አቅምን ይበልጥ በማቀናጀት የበለጸገች ሀገር ለመፍጠር የሚደረገውን ጥረት ለማሳካት የሚረዳ ነው።

ያላቸውን እውቀት ተጠቅመው በተሰማሩበት የስራ መስክ ውጤታማ ለመሆን ቁርጠኛ መሆናቸውንም አስታውቀዋል።   

በስድስተኛው ሃገር አቀፍ ምርጫ አሸናፊ የሆነው የብልጽግና ፓርቲ በመሰረተው መንግስት ውስጥ በጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅራቢነት ሶስት የተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮች የተካተቱበት አዲስ ካቢኔ መመስረቱን ቀደም ብሎ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም