የሐይማኖት ተቋማት ጉባኤ በሱሉልታ ከተማ ለሚኖሩ አቅመ ደካማ ሴቶች ድጋፍ አደረገ

85

መስከረም 28 ቀን 2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ሐይማኖት ተቋማት ጉባኤ በሱሉልታ ከተማ ለሚኖሩ አቅመ ደካማ ሴቶች ድጋፍ አደረገ።

የጉባኤው ጠቅላይ ጸሐፊ ቀሲስ ታጋይ ታደለ በሱሉልታ ከተማ በመገኘት ድጋፉን አስረክበዋል።

ጉባኤው ድጋፉን ያደረገው ከኖርዌይ ቤተክርስቲያን ጋር በመተባበር መሆኑን ጠቅሰው፤ ድጋፉም በዋናነት የሴቶች ንጽሕና መጠበቂያ፣ ሳሙና እና ሳኒታይዘር ያካተተ መሆኑን ገልፀዋል።

ወቅቱ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ እየተስፋፋ ያለበት በመሆኑ በሽታውን ለመከላከልና በዋናነትም ሴቶችን ለማገዝ ያለመ ድጋፍ መሆኑን ተናግረዋል።

አክለውም ድጋፉ ኅብረተሰቡ በየአካባቢያቸው ለችግር የተጋለጡ ዜጎች እንዲደገፉ አርአያ ለመሆን የታሰብ እንደሆነም አንስተዋል።

ድጋፉን የተረከቡት የተፈናቃዮቹ ተወካይ ወይዘሮ ፀሐይ ጌታሁን በበኩላቸው እርዳታው የሴቶችን ችግር በማቃለል ረገድ በጎ ሚና እንዳለው ተናግረዋል።

ጉባኤው ላደረገው ድጋፍ ምስጋና አቅርበው፤ ሌሎች ተቋማትም የጉባኤውን አርአያነት በመከተል ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ሐይማኖት ተቋማት ጉባኤ በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ከቀዬአቸው ለተፈናቀሉ ዜጎች ሰብዓዊ ድጋፍ ለማድረግ ሀብት የማሰባሰብ ስራ እያከናወነ መሆኑ ይታወቃል።