በክልሉ የኮሮና ቫይረስ ነጻ የምርመራ ማዕከላት 34 ደርሷል

119

አሶሳ ፤ መስከረም 28/2014 (ኢዜአ) የኮሮና ቫይረስ ስርጭት ለመከላከል ነጻ የምርመራ ማዕከላትን ቁጥር 34 ማድረሱን የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ጤና ቢሮ አስታወቀ፡፡

በክልሉ አሁንም የኮሮና ቫይረስን በመከላከል ረገድ በህብረተሰቡ ዘንድ  መዘናጋት እንደሚስተዋል ነው ቢሮው ያመለከተው።

የቢሮው ሃላፈ አቶ ፈቃዱ ረጋሳ ለኢዜአ እንዳሉት ፤ ቢሮው ችግሩን ለማቃለል  በአሶሳ ብቻ ተወስኖ የቆየውን የኮሮና ቫይረስ ምርመራ  ማዕከል በቅርቡ በሁሉም የወረዳ ማዕከላት በሚገኙ 30 ጤና ጣቢያዎች እና ሆስፒታሎች አስፋፍቷል፡፡

በክልሉ በሚገኙ አምስት የስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎችና ማረሚያ ቤቶችም አገልግሎቱ እየተሰጠ ነው ብለዋል፡፡

እንዲሁም በአሶሳ ከተማ የሚገኙ አራት የግል ጤና ተቋማት ነጻ የኮሮና ቫይረስ  ምርመራ በቅርቡ መጀመራቸውን አቶ ፈቃዱ አስረድተዋል፡፡

ምርመራ ተደርጎ ቫይረሱ የሚገኝባቸው ሰዎች በመኖሪያ ቤታቸው እንዲያገግሙ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የከፋ ህመም የታየባቸው ደግሞ በአሶሳ፣ ፓዌ እና ካማሽ ሆስፒታሎች  ለይቶ ማከሚያ ማዕከላት  ገብተው ህክምና እያገኙ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

ከአሶሳ ከተማ ነዋሪዎች መካከል አቶ ስሌማን መሃመድ በሰጡት አስተያየት፤ በከተማዋ ህብረተሰቡ ቫይረሱን ለመከላከል የሚያደርጉት ጥንቃቄ እየቀነሰ መምጣቱን እንደታዘቡ ተናግረዋል፡፡

የአፍና አፍንጫ ጭንብል የሚጠቀሙ አንዳንድ ሰዎች የቫይረሱ ተጠቂዎች ተደርገው የሚታዩበት አጋጣሚ እንዳለ ጠቁመው፤  ህብረተሰቡ የመንግስትን ግፊት ሳይጠብቅ ራሱን ከቫይረሱ መከላከል እንዳለበት አመልክተዋል፡፡

በቅርቡ በኮሮና ቫይረስ ተይዘው እንደዳኑ  የገለጹት አቶ ደሬሳ እጀታ በበኩላቸው፤  የጽኑ ህሙማን ክፍል ገብተው በሞትና ህይወት መካከል ሆነው እንዳሳለፉ ያስታውሳሉ፡፡

ለቤተሰቡም ከፍተኛ ጭንቀት እና ድንጋጤ የፈጠረ እንደነበርም አስረድተዋል፡፡

የቫይረሱ መከላከያ ዘዴዎች ተግባራዊ እንዲሆኑ የተጠናከረ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ እንደሚያስፈልግ ነው አቶ ደሬሳ  ያመለከቱት፡፡

በክልሉ እስካሁን ከ27 ሺህ ለሚበልጡ ተጋላጭ የህብረተብ ክፍሎች የኮሮና ቫይረስ መከላከያ ክትባት ተሰጥቷል፡፡

ምርመራ ከተደረገላቸው 44 ሺህ ከሚጠጉ ሰዎች መካከል ከ3 ሺህ 730 በላይ ቫይረሱ እንደተገኘባቸውና  የ30 ሰዎች ህይወት ማለፉን ከጤና ቢሮው የተገኘ መረጃ ያመለክታል፡፡