በጀርመን የሚኖሩ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማህበረሰብ አባላት ለአውሮፓ ፓርላማ የተቃውሞ ደብዳቤ ጻፉ

99

መስከረም 28 ቀን 2014 (ኢዜአ) በጀርመን የሚኖሩ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማህበረሰብ አባላት የአውሮፓ ፓርላማ በኢትዮጵያ ጉዳይ እንዲወያይበት የቀረበ ረቂቅ የውሳኔ ሃሳብን በመቃወም ደብዳቤ ጻፉ።

ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያኑ በደብዳቤያቸው የውሳኔ ሃሳቡ ከርዕሱ ጀምሮ አድሏዊነትን ከማሳየቱም በላይ በርካታ እውነታዎችን ያላገናዘበ እንደሆነ ገልጸዋል።

በደብዳቤው ከተገለጹ ጉዳዮች መካከል የቀረበው ረቂቅ የውሳኔ ሃሳብ በአንድ ክልል ላይ የሚያተኩርና በአፋርና በአማራ ክልሎች ላይ በአሸባሪው ህወሃት የተፈጸመውን ውድመት ሆን ብሎ በመዝለል አድሏዊነት እንዳሳየ አንስተዋል፡፡

“ረቂቁ ለአሸባሪው የህወሃት ቡድን ያደላ እንደሆነ፣ አሸባሪ ቡድኑ የተኩስ አቁም ውሳኔን በመጻረርና ጦርነቱን በማስፋፋት በአፋርና አማራ ክልሎች ስለገደላቸው ንጹሃን ሰዎች ምንም ያለው ነገር የለም” ብለዋል፡፡

ለግጭቱ መነሻ የሆነውንና አሸባሪው ቡድን በሰሜን ዕዝ ላይ የፈጸመውን ጥቃት ሰነዱ መዘንጋቱን፣ በአሸባሪው ቡድን ታግተው ያሉ ከ400 በላይ የዕርዳታ እህል ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች ጉዳይ አለመጠቀሱንም እንዲሁ፡፡

ኢትዮጵያ የአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነትን ስትቀበል አሸባሪው ቡድን ግን ይህን ሃሳብ መቃወሙን ሳይጠቅስ ማለፉን እንዲሁም በቅርቡ የተካሄደውን ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ተከትሎ በኢትዮጵያ አዲስ መንግስት መቋቋሙንና ሁሉን አቀፍ ውይይት ለማድረግ መንግስት ዝግጁ መሆኑን መግለጹን በውሳኔ ሃሳቡ ላይ አለማንሳቱ ጠቅሰዋል፡፡

የአውሮፓ ፓርላማ ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ ያቀረበቻቸውን መረጃዎችና እውነታውን በማገናዘብ እንዲሁም በአውሮፓ ህብረትና በኢትዮጵያ መካከል ለዘመናት ለቆየው ስትራቴጂያዊ አጋርነት ግምት በመስጠት የቀረበውን ረቂቅ የውሳኔ ሃሳብ ዳግም እንዲያጤነውና ውድቅ እንዲያደርገው ጠይቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም