በኢትዮጵያ የተጀመሩ ለውጦች እንዲፋጠኑ የጎረቤት አገራት መተባበር ወሳኝ ነው

አዲስ አበባ ነሀሴ 11/2010 በኢትዮጵያ የተጀመረውን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ለውጥ  ለማፋጠን የጎረቤት አገራት ድጋፍና ትብብር ከፍተኛ ሚና እንዳለው ምሁራን ገለጹ። 'አይን አልጀዚራ' የተባለው የአልጀዚራ አረብኛ ፕሮግራም ጠቅላይ ሚኒትር ዶክተር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ በአገሪቱ የታዩ ለውጦች ላይ ከፖለቲካና ኢኮኖሚ ምሁራንና ተንታኞች ጋር ባደረገው ውይይት ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ከፍተኛ የምጣኔ ሀብት ዕድገት እያስመዘገበች መሆኗን ጠቅሷል። የስልጣን ሽግግር ከተደረገ ጀምሮ ከኤርትራ ጋር የነበረው አለመግባባት በሰላም መፈታቱ፣ በአገር ውስጥ ካሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር የተደረገው ውይይት እንዲሁም በውጭ አገር የሚኖሩ ተቃዋሚዎች ወደ አገር እንዲመለሱ መደረጉ፣ ተዘግተው የነበሩ የመገናኛ ብዙኃን መከፈታቸውን አድንቀዋል። በቀጣናው ያለው የፖለቲካና የኢኮኖሚ ለውጦች ይበልጥ እንዲፋጠን የጎረቤት አገራት ድጋፍና ትብብር ከፍተኛ ሚና እንዳለው ምሁራኑና ተንታኞቹ አብራርተዋል። የኢትዮጵያ ሰላምና መረጋጋት እንዲሁም ከጎረቤት አገራት ጋር ያላት መልካም ግንኙነት ለቀጣናው ሰላም አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ገልጸዋል። ኢትዮጵያና ኤርትራ የሰላም ስምምነት ካደረጉ በኋላ የቀጣናው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እየተሻሻለ እንደመጣ ጠቅሰው ከአስር ዓመት በኋላ በኤርትራና በሶማሊያ መካከል የተጀመረው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ተጠቃሽ ነው ብለዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ በአገር ውስጥና በጎሮቤት አገራት የወሰዷቸው የለውጥ እርምጃዎች ለቀጠናው መረጋጋት ጉልህ አስተዋጽኦ እንዳለው ብዙዎች አረጋግጠዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም