የካቢኔ መዋቅሩ የተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮችን ማካተቱ ለአገሪቷ የለውጥ ጉዞ መጎልበት የጎላ ሚና ይኖረዋል

71

ጊምቢ ፣ መስከረም 28/2014 (ኢዜአ) የካቢኔ መዋቅሩ የተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮችን ማካተቱ ለአገሪቷ የለውጥ ጉዞ መጎልበት የጎላ ሚና እንደሚኖረው የምዕራብ ወለጋ ዞን ነዋሪዎች ገለጹ።

በመንግስት ምስረታው ልምድ ያካበቱ ኣመራሮችና ተፎካካሪ ፓርቲዎችን ማካተቱ የሰለጠነ ፖለቲካ መልካም ጅማሮ ነው ብለዋል።

ወጣት ቢቂላ ዋቅሹማ ለኢዜአ እንደተናገረው ይህ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተሰጠው ሹመት አካታች የሆነ የፖለቲካ መልካም ጅምር መሆኑን ይገልጻል።

“ይሄ ጅምር ስራ ለሃገር እድገትና ለዴሞክራሲ ምህዳር መስፋት ትልቅ አስተዋፅኦ ስላለው ለስኬቱ የሚመለከተው ሁሉ መስራት አለበት” ብሏል።

በተለይም ወጣቶች አጠናክረው ለሃገር ዘላቂ ልማትና አንድነት መረጋገጥ በሚያደርጉት ትግል ውስጥ እሱም የድርሻውን ለማበርከት ዝግጁ መሆኑን ተናግሯል።

የጊምቢ ከተማ ነዋሪው አቶ ቀጄላ ለሜሳ እንዳሉት ተሿሚዎቹ ሃገር ለማፍረስ የተነሱ አሸባሪዎችን በማስወገድ ለእድገትና ብልጽግና ተግተው መስራት እንደሚጠበቅባቸው ተናግረዋል።

አዲስ ከተመሰረተው መንግስት ጎን በመሆንም የሚጠበቅባቸውን ድጋፍ እንደሚያደርጉም አቶ ቀጀላ አመልክተዋል፡፡

የመንዲ ከተማ ከንቲባ አቶ ፈቀዴ ታሲሳ እንደገለፁት በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተሰጠው ሹመት ለአንድ አገር የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ መሰረት የጣለ መሆኑንና ለተጀመረው የለውጥ ጉዞ መጎልበት የጎላ ሚና እንዳለው ተናግረዋል።

ይህ በጎ ጅምር አገሪቷን ወደተሻለ ደረጃ የሚያሻግር በመሆኑ ሁሉም በአንድ መንፈስ ከመንግስት ጎን በመቆም ለሃገር ግንባታ የሚጠበቅበትን ሁሉ ማበርከት እንዳለበት አሳስበዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ በአገሪቷ ጠንካራ የዴሞክራሲ ስርዓት እንዲገነባ እያደረጉ ያለው ጥረት ለአገራችን አዲስና የመጀመሪያ ከመሆኑም በላይ በቃል የተናገሩትን በተግባር የሚያሳዩ መሆኑን አመላካች ነውም ብለዋል ነዋሪዎቹ::

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም