የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎትን ለማሻሻል የሁሉም የጸጥታ አካላት ተሳትፎ ወሳኝ ነው

132

አዳማ፣ መስከረም 28 ቀን 2014 (ኢዜአ) የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጡን የተቀላጠፈ ለማድረግ በየደረጃው ከሚገኙ የፀጥታ አካላትና ህብረተሰቡ ጋር በትብብር እየሰራ እንደሚገኝ የኢትዮ-ጂቡቲ ባቡር አክሲዮን ማህበር ገለፀ።

የአክሲዮን ማህበሩ ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ጥላሁን ሳርካ በአዳማ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት ከውጭ የሚገቡ እቃዎችን 50 በመቶ ከወደብ ማንሳት ተችሏል።

“አንድ ባቡር ጂቡቲ ደርሶ ለመመለስ 24 ሰዓት ይወስድበታል” ያሉት ኢንጂነር ጥላሁን፤ “በአንድ ጊዜ ጭነት ብቻ 53 ተሽከርካሪዎች ከነተጎታች የሚጭኑትን ኮንቴይነር በማንሳት ከሳምንት በላይ በተሽከርካሪ የሚፈጀውን የወደብ ላይ የኮንቴይነር ቆይታ ወደ አንድ ቀን ማውረድ ችለናል” ብለዋል።

በዚህም ከ10 ሚሊዮን ቶን በላይ የወጪና የገቢ እቃዎችን ማጓጓዝ መቻሉን ጠቅሰው፤ አገልግሎቱን ይበልጥ ለማሳለጥ የምክክር መድረኩ ማስፈለጉንም አመልክተዋል።

የባቡሩ ደህንነትና የፀጥታ ሁኔታ ሲረጋገጥ አገልግሎቱ እንደሚቀላጠፍ ገልጸው፤ ለዚህ ደግሞ የባቡር መስመሩ የሚያልፍባቸው ዞኖችና ወረዳዎች ወሳኝ ሚና እንዳላቸው ጠቁመዋል።

በተለይ የባቡር እገታ፣ በመስመሩ ላይ እንስሳት መልቀቅ፣ የእግረኛ ማቋረጫ ትቶ በሃዲድ ላይ መጓዝ በዘርፉ እያገጠመ ያለው ቁልፍ ችግር መሆኑን ገልጸዋል።

“በሃዲዱ ላይ የሚፈፀም ስርቆት ከአዲስ አበባ እስከ ሚኤሶ ባለው የባቡር መስመር ላይ እየተስተዋለ ነው” ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ችግሩን ለመፍታት በባቡር መስመሩ ግራና ቀኝ ከሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር እየተሰራ እንደሆነ ተናግረዋል።

በዚህ ረገድ የአካባቢው የጸጥታ አካላት ተሳትፎ እንዳላቸውም ጠቁመዋል።

የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎትን ለማቀላጠፍ በመስመሩ ላይ የሚፈፀሙ ስርቆትንና ተያያዥ ወንጀልን ለመቆጣጠር ከአክሲዮን ማህበሩ ጋር እየሰሩ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የሞጆ ከተማ ፀጥታ ጽሕፈት ቤት ሃላፊ አቶ አዱኛ ሚዳቅሶ ናቸው።

አክሲዮን ማህበሩ የአገልግሎት መስተጓጎል እንዳይፈጠር የህብረተሰቡን ግንዛቤ ከማሳደግ ጀምሮ በየደረጃው ካሉ የፀጥታ አካላት ጋር በትብብር ለመስራት እያደረገ ያለውን ጥረት እንዲያጠናክር ጠይቀዋል።

የአዋሽ አርባ ፖሊስ መምሪያ አዛዥ ኢንስፔክተር ኤዶም ኢብራሂም በበኩላቸው አክሲዮን ማህበሩ ህብረተሰቡን ያሳተፈ ስራ ለመስራት መዘጋጀቱን አድንቀዋል። የባቡር መስመሩ ላይ እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችን በመተባበር ለመፍታት እየተሞከረ እንደሆነ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም