በነገሌ ከተማና በምዕራብ ወለጋ ላሎ አሳቢ ወረዳ ለችግረኛ ህፃናት የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ተሰጠ - ኢዜአ አማርኛ
በነገሌ ከተማና በምዕራብ ወለጋ ላሎ አሳቢ ወረዳ ለችግረኛ ህፃናት የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ተሰጠ

ነገሌ/ግምቢ መስከረም 27/2014 (ኢዜአ) የነሌ ከተማና በምዕራብ ወለጋ ዞን በላሎ አሰቢ ወረዳ ለሚገኙ 371 የችግረኛ ቤተሰብ ህፃናት የትምህርት መርጃ ቁሳቁና የደንብ ልብስ ተበረከተ፡፡
የነገሌ ከተማ ትምህርት ጽህፈት ቤቱ ሃላፊ አቶ ተስፋዬ በዛብህ በከተማው ለሚገኙ 181 ተማሪዎች ባጠቃላይ 2 ሺህ 181 ደብተር፣ 543 እርሳስና እስክሪብቶ፣ 15 የደንብ ልብስ ድጋፍ መደረጉን ገለጹ።
እንደ ሃላፊው ገለጻ ከተጠቀሱት ተማሪዎች በተጨማሪ ለአንድ አካል ጉዳተኛ ተማሪ የመንቀሳቀሻ ወንበር(ዊልቼር) ድጋፍም ተደርጓል።
ስጦታው የተበረከተው በእድሜ መግፋትና በአካል ጉዳት መስራት ለማይችሉና በዝቅተኛ ገቢ ለሚተዳደሩ ወላጆች ህጻናት እንደሆነም ነው የተናገሩት።
ድጋፉ ከነገሌ ከተማ በጎ ፈቃደኛ ነጋዴዎች፣ ከመንግስት ሰራተኞችና ከተለያዩ ሴክተር መስሪያ ቤቶች የተሰበሰበ እንደሆነም አብራርተዋል፡፡
የጉጂ ዞን ትምህርት ጽህፈት ቤት ሃላፊ ተወካይ አቶ በሃይሉ ብሩ “እኛ ኢትዮጵያዊያን እርስ በእርስ በመረዳዳትና በመደጋገፍ የችግር ቀንን የማለፍ የአኩሪ ባህል ባለቤት ነን” ብለዋል፡፡
በዞኑ በዚህ አመት ብቻ 520 ሺህ መደበኛ ተማሪዎችን ለመቀበል ዝግጀት ተጠናቆ የተማሪዎቹ ምዝገባ እየተካሄደ እንደሆነም አስረድተዋል።
ትምህርትን ለሁሉም ተደራሽ ለማድረግ በተለይም የተቸገሩ ወገኖችን ለማገዝ የተጀመረው ድጋፍና ትብብር ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል።
በተመሳሳይ ዜና በምዕራብ ወለጋ ዞን በላሎ አሰቢ ወረዳ ላሉ 190 የችግረኛ ቤተሰብ ተማሪዎች የትምህርት መማሪያ ቁሳቁስ ድጋፍ ተደረጓል።
የላሎ አሳቢ ወረዳ ሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ጽህፈት ቤት ሃላፊ ወይዘሮ መሰረት ዳንኤል እንዳሉት በመማሪያ ቁሳቁስ እጦት ምክንያት ከትምህርት ገበታ ውጭ እንዳይሆኑ በተሰራው ስራ ለተማሪዎቹ ድጋፉን ማድረስ ተችሏል።
ድጋፉ ከወረዳው የመንግስት መስሪያ ቤቶችና ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተሰበሰበ መሆኑን ነው ሃላፊዋ የገለጹት።
ከድህነትና ከኑሮ ውድነት የተነሳ በርካታ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው እንዳይቀሩ በተሰራው ስራ አበረታች ውጤት መገኘቱን የተናግሩት ሃላፊዋ ዛሬ የተደረገው ድጋፍ 100ሺህ ብር የሚገመት የትምህርት ቁሳቁስ እንደሆነም ገልጸዋል።
ድጋፍ የተደረገላቸው ተማሪዎችም በተበረከተላቸው ስጦታ መደሰታቸውን ገልፀው ትምህርታቸውን ጠንክረው በመማር ለራሳቸውና ለአገራቸው ቁምነገር ለመስራት ህልም እንዳላቸው ተናግረዋል።
ተማሪ አብዲ ጂራታ እንዳለው በተደረገለት ድጋፍ መደሰቱን ገልጾ ትምህርቱን ጠንክሮ በመማር ነገ የተሻለ ቦታ ላይ ደርሶ እንደ እሱ ድጋፍ ለሚፈልጉ ህጻናትን ለመርዳት እንደሚፈልግ ተናግሯል።
የተደረገለት ድጋፍ ይሄንን ህልሙን ለማሳካት ትልቅ እገዛ እንደሆነ ገልጾ ዋናው ትኩረቱ ትምህርቱን ውጤታማ ማድረግ እንደሆነ ተናግሯል።
ተማሪ ጫልቱ ደረጀ በበኩሏ የትምህርት ቁሳቁስ ዋጋ ውድ በመሆኑና ቤተሰቦቿም መግዛት ሰለማይችሉ የ2014 የትምህርት ዘመንን ከትምህርት ገበታዋ ልትለይ እንደነበረ ተናግራለች።
አሁን የተደረገለላት ድጋፍም የልጅነት ምኞቷን እንድታሳካ ጠንክራ መማር የምትችልበትን እድል ያመቻቸ መሆኑን ገልጻለች።