ዋሊያዎቹ ከሴራሊዮን አቻቸው ጋር የሚያደርጉትን ጨዋታ የሚመሩ ዳኞች ይፋ ሆኑ

1226

አዲስ አበባ ነሀሴ 11/2010 የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን (ዋሊያዎቹ) ከሴራሊዮን አቻቸው ጋር የሚያደርጉትን ጨዋታ የሚመሩት ዳኞች ታወቁ።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው፤ ዋሊያዎቹ በመጪው ጳጉሜ 4 ቀን 2010 ዓ.ም ከሲራሊዮን አቻቸው ጋር በሐዋሳ ዓለም አቀፍ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

በ2011 ዓ.ም በካሜሮን በሚካሄደው 32ኛው አፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ ዋሊያዎቹ ከሴራሊዮን ጋር የሚያደርጉትን ጨዋታ የሚመሩት ዳኞች ታውቀዋል።

በዚህም መሰረት ጨዋታውን በዋና ዳኝነት ቱኒዚያዊው ሳዶክ ሴለሚ ሲመሩት በኮሚሽነርነት ደግሞ ማሞን ቤሻራ ናሳራ ከሱዳን ተመርጠዋል።

እንዲሁም አቲያ አምሳድ ከሊቢያ፣ ሲሊስቲያን ታንጉንጊ ከሩዋንዳ፣ አያሜን ኢስማኤልና ናስራለህ ጀዋዲ ከቱኒዚያ በረዳት ዳኝነት እንደሚመሩ ታውቋል።

ብሔራዊ ቡድኑም በጋና አቻው 5 ለ 0 ከተሸነፈ በኋላ ጳጉሜ ላይ ከሴራሊዮን ጋር ሁለተኛ የማጣሪያ ጨዋታውን የሚያካሂድ ይሆናል።

ለዚሁ ጨዋታ ዝግጅት በኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ የሚመራው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዝግጅቱን በሐዋሳ እያደረገ ይገኛል።

በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ኢትዮጵያ በምድብ 5 ከጋና፣ ኬንያና ሴራሊዮን ጋር ተደልድላለች።