የአዋሽ-ኮምቦልቻ-ሐራ ገበያ የባቡር መስመር ዝርጋታ ፕሮጀክት በህወሓት የሽብር ቡድን ወደመ

40

ደሴ፤ መስከረም 27/2014 (ኢዜአ) የአዋሽ-ኮምቦልቻ-ሐራ ገበያ የባቡር መስመር ዝርጋታ ፕሮጀክት በህወሓት የሽብር ቡድን ከፍተኛ ውድመት እንደደረሰበት የፕሮጀክቱ ስራ አስኪያጅ አስታወቁ።
 የፕሮጀክቱ ስራ አስኪያጅ ኢንጅነር አብዱል ከሪም መሐመድ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ የፕሮጀክቱን ግንባታ በ2015 ዓ.ም በማጠናቀቅ ስራ ለማስጀመር ታስቦ 24 ሰዓት እየተሰራ ነበር።

በሁለት ምዕራፍ ተከፍሎ ስራው  ከነበረው ፕሮጀክቱ የመጀመሪያው ምዕራፍ አዋሽ-ኮምቦልቻ 270 ኪሎ ሜትር 99 በመቶ፤ ሁለተኛው ምዕራፍ ደግሞ ከኮምቦልቻ-ሐራ ገበያ 120 ኪሎ ሜትር 83 በመቶ መጠናቀቁን አስረድተዋል።

በተለይ ከኮምቦልቻ-ሐራ ገበያ ያለውን መስመር  ለማጠናቀቅ በፕሮጀክቱ አካባቢ በሚገኙ ስድስት  ካምፖች ዘመናዊ ማሽኖችና ቁሳቁሶች ገብተው ርብርብ ሲደረግ እንደነበር አስታውሰዋል።

ሆኖም አራቱ ካምፖች  በአሸባሪው የህወሓት ቡድን   ንብረት ለዝርፊያ፣ ውድመትና ብልሽት መዳረጋቸውን  አስታውቀዋል።

 268 እስካባተር፣ ዶዘር፣ ገልባጭ ተሽከርካሪ ፣ ዳም ትራክና ሌሎች ማሽኖች በካምፖቹ ውስጥም  እንደነበሩ ጠቁመው፤ ''የቻሉትን ዘርፈው ያልቻሉትን ደግሞ አውድመውታል'' ብለዋል፡፡

''ሁሉንም ካምፖች ተዘዋውረን የማየት እድል ባይገጥመንም  መሰረተ ልማቱና ንብረቶች መውደማቸውን ከአይን እማኞች ማረጋገጥ ችለናል'' ነው ያሉት።

ከሽብር ቡድኑ ነጻ የወጣውን አንድ ካምፕ በአካል ተገኝተው መመልከታቸውን የጠቆሙት ፤ኢንጅነር አብዱል ከሪም ፤ካምፑ  ሙሉ በሙሉ መውደሙንና መዘረፉን አረጋግጠዋል።

የፕሮጀክቱን  የዋሻ መስመሮች እንደ ምሽግ፣ድልድዮችን ደግሞ ለታንክና ከባድ ተሸከርካሪዎች መሸጋጋሪያ በማድረጋቸው የሀዲድ መስመሩ  ለጉዳት ማዳረጉንም ጠቅሰዋል፡፡

ከስድስት ዓመት በላይ የተደከመበት ግዙፍ ፕሮጀክት በዚህ መልኩ መውደሙ እንዳሳዘናቸው ገልጸዋል።

በፕሮጀክቱ መውደም  የሰራተኛውን ሞራልና ስነ ልቦናም ከመጉዳቱ ባለፈ ስራው በመቆሙ ምክንያት ከ3 ሺህ በላይ ሰራተኞች እንዲበተኑ መደረጉን ኢንጅነር አብዱል ከሪም ተናግረዋል።

ቡድኑም ላደረሰው  እያንዳንዱ ጥፋት  በህግ ተጠያቂ ማድረግ እንደሚገባ ያመለከቱት ስራ አስኪያጁ ፤ ''አካባቢው ነጻ ከወጣ በእልህና በቁጭት በአጭር ጊዜ የፕሮጀክቱን ስራ አጠናቀን  ስራ ለማስጀመር ቁርጠኛ ነን'' ብለዋል።

አዋሽ-ኮምቦልቻ-ሐራ ገበያ ባቡር ፕሮጀክት በአንድ ነጥብ 7 ቢሊዮን ዶላር ወጪ ለመገንባት ስራው የተጀመረው በ2007 ዓ.ም እንደሆነ ተመለክቷል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም