በሽታን አስቀድሞ በመከላከልና በመቆጣጠር ረገድ ውጤት እየመጣ ነው

71

አዳማ፣ መስከረም 27/2014( ኢዜአ ) ብሔራዊ የጤና ደህንነት ስትራቴጂና መርሃ ግብር በሽታን አስቀድሞ በመከላከልና ከተከሰተም በመቆጣጠር ረገድ ውጤት እያመጣ መሆኑን የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ገለፀ።

ኢንስቲትዩቱ የተጠናቀቀው በጀት ዓመት ብሔራዊ የጤና ደህንነት ድርጊት መርሃ ግብር አፈፃፀምና የተገኙ ውጤቶች ላይ በአዳማ ከተማ ከባለድርሻ አካላት ጋር እየመከረ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አስቻለው አባይነህ እንደገለጹት ብሔራዊ የጤና ደህንነት መርሃ ግብር በሽታን አስቀድሞ በመከላከልና ከተከሰተም በመቆጣጠር ረገድ ውጤት እያመጣ ነው።

ብሔራዊ የጤና ደህንነት ስትራተጂና መረሃ ግብር በሀገሪቷ ሊኖር የሚችሉ የጤና ስጋቶችን ለመከላከልና በሽታዎች ከተከሰቱም ለመቆጣጠር የሚያስችል አቅም ለመገንባት የሚያስችል እንደሆነም ተናግረዋል።

በዚህም ባለፉት ሁለት ዓመታት የኮሮና ወረርሽኝን ከመከላከልና ከመቆጣጠር ብሎም ሌሎች ለጤና አደጋ ሊሆኑ የሚችሉ ስጋቶችን ከመቀነስ አንፃር ውጤት መመዝገቡን ገልጸዋል።

በተለይ በብሔራዊ የጤና ስትራቴጅና መርሃ ግብር ባለድርሻ አካላትና ሴክተሮች ያሳዩት ትብብርና ቅንጅት ኮሮናን በመከላከል ረገድ ሀገራችን ትልቅ ውጤት ያሳየችበት መሆኑን ተናግረዋል።

ስትራተጂውን ግብርና፣ ትምህርት፣ ጤናና ሌሎች ተቋማትን ጨምሮ 17 ሴክተር መስሪያ ቤቶች በባለቤትነት እንዲያስፈፅሙ አቅጣጫ መቀመጡንም አቶ አስቻለው ገልፀዋል።

“በሚቀጥሉት ሶስት ዓመታት ሊከሰቱ የሚችሉ ወረርሽኞችን ጨምሮ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎችን ለመከላከልና ተፅዕኖውን ለመቋቋም የሚያስችል አቅም በመገንባት ላይ በትኩረት ይሰራል” ብለዋል።

“በተለይ በምርምርና በዘመናዊ ላቦራቶሪ የተደገፈ የበሽታዎች ቅኝትና አቅም ግንባታ፣ በበሽታዎችም ሆነ በሰው ሰራሽና በተፈጥሮ አደጋ ሊመጡ የሚችሉ ችግሮችን አስቀድመን በመለየትና የመከላከል ስርዓት መዘርጋት ቀጣይ የሚጠብቀን ተግባር ነው” ብለዋል።

ኮሮናን ለመከላከልና አቅም ለመፍጠር በተደረገው ርብርብ በሀገሪቷ አንድም ያልነበረውን የኮሮና ምርመራ ላቦራቶሪ 85 ማድረስ መቻሉን ጠቅሰው ዩኒቨርሲቲዎችን ጨምሮ የግሉ የህክምና ሴክተር በቅንጅት እንዲሰሩ በመደረጉ ጥሩ ውጤት አግኝተናል ነው ያሉት።

የተሟላ መረጃን በተገቢው መንገድ ያለመያዝና ለማህበረሰቡ በወቅቱ ተደራሽ ማድረግና የህብረተሰብ ጤና ማስተባበሪያ ማዕከል በክልሎች በተገቢው መንገድ አስቀድሞ ያለማደራጀት የታዩ ክፍተቶች እንደነበሩ ጠቅሰዋል።

የዘርፈ ብዙ ሴክተሮች ቅንጅት ጠንካራና መዋቅራዊ ያለመሆን፣ የብሔራዊ ጤና ደህንነት ምክር ቤት ያለመኖር በዘርፉ የታዩ ሌሎች ክፍተቶች እንደሆኑም ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የዓለም የጤና ደንብ ተጠሪ ዶክተር ፈይሳ ረጋሳ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ብሔራዊ የጤና ደህንነት ከማረጋገጥ አኳያ ስትራተጂና የድርጊት መርሃግብር ተግባራዊ በማድረግ ውጤታማ መሆኗን ተናግረዋል።

በተለይ የኮሮና ወረርሽኝን ለመከላከል የወሰደችው እርምጃ የስትራተጂው አንዱ ውጤት መሆኑን ጠቅሰው፣ አሁን ከኮሮና በኋላ ሊኖሩ የሚችሉ በሽታዎችን አስቀድሞ ለመከላከልና ከተከሰቱም ለመቆጣጠር ሁሉንም ሴክተሮች ያከተተ ስራ መስራት ይኖርበታል ብለዋል።

አሁን ሀገሪቷ የላቦራቶሪ አቅም ከመገንባት፣ የድንገተኛ ማዕከላት ከማደረጀትና ወደ ስራ ከማስገባት አንፃር የተሻለ ስራ የሰራች ቢሆንም በየጊዜው ክትትል፣ ቁጥጥርና ግምገማ በማድረግ ላይ ክፍተት መኖሩን ተናግረዋል።

ለሶስት ቀናት በሚካሔደው በዚህ መድረክ ላይ የኢንስቲትዩቱን አመራሮችና ባለሙያዎች ጨምሮ ከተለያዩ ተቋማት የተውጣጡ ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ይገኛሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም