የኮንትሮባንድ ችግር ካለው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር ባሻገር የደህንነት ስጋት እየሆነ መጥቷል

193
አዲስ አበባ ነሀሴ 11/2010 ኮንትሮባንድ ካለው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር ባሻገር የደህንነት ስጋት እየሆነ መምጣቱን የኢትዮጵያ የገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ገለጸ። ባለስልጣኑ በአገሪቷ የሚስተዋለውን የኮንትሮባንድ ንግድ ለመከላከል ባደረገው ጥረት ባለፉት አምስት ዓመታት በኮንትሮባንድ ወደ አገር ውስጥ ሊገባ ከነበረ እቃ 3 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር እንዲሁም ወደ ወጪ በኮንትሮባንድ ሊላክ ከነበረ እቃ 535 ሚሊዮን ብር በቁጥጥር ስር ማዋሉን አስታውቋል። የባለስልጣኑ የህግ ማስከበር ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ዘመዴ ተፈራ ለኢዜአ እንደገለጹት በአገሪቷ ስር የሰደደው የኮንትሮባንድ ንግድ እንቅስቃሴ ካለው የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር ባሻገር የደህነነት ስጋት እየሆነ ነው። የኮንትሮባንድ ዓይነቶች ከአገር የሚወጡና ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ ሲሆኑ እነዚህም ወደ አገር እንዳይገቡ የተከለከሉ፣ ገደብ የተደረገባቸው፣ አስፈላጊው ቀረጥ ተከፍሎ በጉሙሩክ ስነ ስርዓቱ ውስጥ ያላለፉ ምርቶች በዋናነት ይጠቀሳሉ። ኮንትሮባንድ  የሚከናወንባቸው ቦታዎች ሰሜናዊ ምዕራብና ደቡባዊ ምስራቅ የአገሪቷ አካባቢዎች መሆናቸውን ጠቅሰው፤ ህገ ወጥ ነጋዴዎቹ ከአገር በሚያስወጧቸው ምርቶች  በመታገዝ ለደህንነት ስጋት የሆኑ የጦር መሳሪያዎችን ወደ አገር ያስገባሉ ብለዋል። ይህም በአገሪቷ በአንዳንድ አካባቢዎች ለሚነሱ ግጭቶችና የሰላም እጦቶች አንዱ ምክንያት ነው ሲሉ አቶ ዘመዴ ተናግረዋል። ባለፉት አምስት ዓመታት የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴን ለመከላከል በተደረገው ጥረት በገቢ ኮንትሮባንድ 3 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብርና በወጪ ኮንትሮባንድ ደግሞ 535 ሚሊዮን ብር የሚገመት ንብረትና የብር ኖቶች በቁጥጥር ስር ውለዋል። ይህም ደረጃቸውን ያልጠበቁ ሸቀጣ ሸቀጦች፣ የህብረተሰቡን ጤና የሚጎዱ መገልገያዎችና ወጣቱን ወደ አልባሌ ሱስ የሚመሩ አደንዛዥ እፆች እንዲገቡ ብቻ ሳይሆን አገሪቷ የውጭ ምንዛሬ እንድታጣም እያደረጋት ይገኛል ሲሉ ገልጸዋል። በ2010 ዓ.ም በኮንትሮባንድ ከአገር ሊወጡ ሲሉ በቁጥጥር ስር ከዋሉት 176 ሚሊዮን የሚገመት ንብረቶች መካከል 139 ሚሊዮኑ የገንዘብ ኖት ነው። እነዚህ የገንዘብ ኖቶች ከአገር በህገ ወጥ መንገድ ወጥተው ወደ አገር ውስጥ በህገ ወጥ መንገድ የሚገቡትን የኮንትሮባንድ እቃዎች ፋይናንስ ለማድረግና ገንዘብ ለማሸሽ እየዋለ መሆኑንም ገልጸዋል። በቀጣይ የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴን ለመግታትም የመከላከል አቅም ማሰደግ፣ የውስጥ አደረጃጀትን ማጠናከር፣ የአሰራር ሥርዓት ማስተካከያ ጥናቶችን መተግባርና አመራሩ ቅንጅታዊ አሰራርን በባለቤትነት አንዲመራ ማድረግ እንደሚገባ አውስተዋል። በተለይ በኮንትሮባንድ እንቅስቃሴ ላይ ህይወታቸውን ጥገኛ አድርገው የሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍሎች ከህገ ወጥ የንግድ እንቅሰቃሴ እንዲላቀቁ የሚያደርግ የሥራ ዕድል ፈጠራና የልማት ሥራ ከባለድርሻ አከላት ጋር እየተሰራ ይገኛል ሲሉም አስታውቀዋል። በኢትዮጵያ በወጭ ኮንትሮባንድ በ2006 ዓ.ም 27 ሚሊዮን ብር፣ በ2007 ዓ.ም 33 ሚሊዮን ብር፣ በ2008 ዓ.ም 141 ሚሊዮን ብር፣ በ2009 ዓ.ም 156 ሚሊዮን ብር እና በ2010 ዓ.ም ደግሞ 176 ሚሊዮን ብር የሚገመት ንብረትና የብር ኖት ከአገር ሊወጣ ሲል በቁጥጥር ሥር ውሏል። ከገቢ ኮንትሮባንድ ደግሞ በ2006 ዓ.ም 415 ሚሊዮን ብር፣ በ2007 ዓ.ም 424 ሚሊዮን ብር፣ በ2008 ዓ.ም 763 ሚሊዮን ብር፣ 2009 ዓ.ም 778 ሚሊዮን ብር እና በ2010 ዓ.ም ደግሞ 827 ሚሊዮን ብር የሚገመት ንብረትና የብር ኖት ወደ አገር ሲገባ በቁጥጥር ሥር መዋሉን ከባለስልጣኑ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም