በአእምሮ ህመም ዙሪያ በማህበረሰቡ ዘንድ ያለውን የተዛባ አመለካከት ለማስተካከል ብዙ መስራት ያስፈልጋል

94

አዲስ አበባ፣ መስከረም 27/2014 (ኢዜአ) በአእምሮ ህመም ዙሪያ በማህበረሰቡ ዘንድ ያለውን የተዛባ አመለካከት ለማስተካከል ብዙ መስራት የሚያስፈልግ መሆኑን የህክምና ባለሙዎች ተናገሩ።
በኢትዮጵያ አብዛኛው ማህበረሰብ በአእምሮ ታማሚዎች ላይ የተሳሳተ ትርጉም በመያዝ መገለል የሚያደርስ መሆኑንም ባለሙያዎቹ ይናገራሉ።

በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ህክምና ኮሌጅ የስነ አእምሮ ትምህርት ክፍል ሳይኮለጂስትና መምህርት ሶሊያና ግዛው በአእምሮ ህመም ዙሪያ በማህበረሰቡ ዘንድ ያለውን የተዛባ አመለካከት ለማስተካከል ብዙ መስራት ያስፈልጋል ይላሉ።

በህብረተሰቡ ዘንድ በአብዛኛው ለአዕምሮ ህክምና የሚሰጠው ቦታ ማነስና የተሳሳተ አመለካከት መያዝ ለችግሩ መባባስ ምክንያት ሆኗል ብለዋል።

የአእምሮ ህክምና እንደማንኛውም በሽታ ታክሞ የሚድን መሆኑን የገለጹት ባለሙያዋ ታማሚዎች የቅርብ ክትትል ማድረግ እንዳለባቸው ጠቁመዋል።

ማህበረሰቡም በአእምሮ ታካሚዎች ላይ "እብድ" የሚለውን የተሳሳተ መጠሪያ በመተው የአእምሮ ታካሚዎችን መደገፍና መንከባከብ ይገባል ብለዋል።

የአእምሮ ህመም በእምነትና መንፈሳዊ ህክምና ብቻ ነው የሚድነው በሚል ዘመናዊ ህክምና እንዳይከታተሉ ማድረግም ተገቢ አለመሆኑን ጠቁመዋል።

የአእምሮ ህመምተኞችን በማቅረብና ማህበራዊ ድጋፎችን በማድረግ ማህበረሰቡ የደርሻውን እንዲወጣ ጠይቀዋል።

በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ህክምና ኮሌጅ የስነ አእምሮ ትምህርት ክፍል መምህር አቤል ወልደሚካኤል፤ በማህበረሰቡ ዘንድ ለአዕምሮ ህመም መባባስ ምክንት የሆኑና መስተካከል ያለበናቸው የተዛቡ አመለካከቶች መኖራቸውን ጠቁመዋል፡፡

በብዙዎች ዘንድ የአእምሮ ህመምን "የሰይጣን ስራ" አድርጎ በመውሰድ ወደ ዘመናዊ ህክምና አለመውሰድ በስፋት ይስተዋላል ብለዋል።

ከበሽታው ለመዳን የእምነትና ባህላዊ ህክምናዎች እንዳሉ ሆነው ማህበረሰቡ ለዘመናዊ ህምክናም ትኩረት እንዲያደርግ መክረዋል።

በኢትዮጵያ የአዕምሮ ጤና እክል ካለባቸው ሰዎች መካከል ዘመናዊ ሕክምና ለማግኘት የሚሄዱት ከ10 በመቶ ያልበለጡ መሆናቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ።

በዓለም አቀፍ ደረጃ በአንድ ቤተሰብ ውስጥ ከሚኖሩ አምስት ሰዎች መካከል አንዱ የአዕምሮ ጤና እክል ችግር ሊያጋጥመው እንደሚችል ይነገራል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም