የፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ፋውንዴሽን ተመሠረተ

829

አዲስ አበባ፣ መስከረም 27/2014 (ኢዜአ)  የፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያምን ራዕይና ስራዎች ለማስቀጠል በስማቸው ፋውንዴሽን ተመሰረተ።

የፕሮፌሰር መስፍንን አንደኛ ዓመት ዝክረ መታሰቢያና የፋውንዴሽኑን ምስረታ አስመልክቶ አዘጋጅ ኮሚቴው ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።

የፋውንዴሽኑ ሊቀመንበር ዶክተር በድሉ ዋቅጅራ ፕሮፌሰር መስፍን ሙሉ ሕይወታቸውን ለአገራቸው የሰጡ ታላቅ ባለውለታ መሆናቸውን አንስተዋል።

ለኢትዮጵያ ልማትና ሰላም፤ ለዜጎች ሠብዓዊ መብት መከበርና የሕግ የበላይነት የነበራቸው አስተዋፅኦ ላቅ ያለ እንደነበርም አስታውሰዋል።

በመሆኑም ይህንን ስራቸውን ለማስቀጠል የሚያስችል ፋውንዴሽን መመስረቱን ጠቅሰዋል።

ፋውንዴሽኑ ከፖለቲካ፣ ከሃይማኖት እና ጎሳ ወገንተኝነት በፀዳ መልኩ አገራዊ ራእያቸውን ለማስቀጠል የተቋቋመ ሲሆን በቤተሰቦቻቸውና እርሳቸውን በሚደግፉ ግለሰቦች እውን መሆኑን ተናግረዋል።

ፋውንዴሽኑ በአገር ውስጥና በውጭ ካሉ በጎ-አድራጊዎች በሚገኝ ገቢና ከአባላቱ በሚሰበሰብ ገንዘብ እየታገዘ በቦርድ የሚመራ መሆኑን ዶክተር በድሉ ገልጸዋል።

ፋውንዴሽኑ በማኅበረሰብ ሳይንስና በሠብዓዊ መብት ላይ ምርምር ለሚያካሂዱ ዜጎች ድጋፍ የሚያደርግ ሲሆን ዓመታዊ አውደ ጥናት በማዘጋጀት የጥናትና ምርምር ስራዎች እንዲካሄዱ ያደርጋልም ነው ያሉት።

በውጭ ካሉ ደጋፊዎች ጋር በመሆን በተለያዩ አገራት አውደ ጥናቶች እንዲካሄድ በማድረግ እንዲሁም አመታዊ የስነፅሁፍና የግጥም ውድድር በማድረግ ሽልማት ይሰጣል ነው ያሉት።

ከሁለት ቀን በኋላ የፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም የሙት አመት ዝክር እንደሚከናወንም አዘጋጅ ኮሚቴው ገልጿል።

መምህር፣ የሰብአዊ መብት ተሟጋች፣ ፖለቲከኛ እንዲሁም ደራሲ የነበሩት ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ባለፈው ዓመት መስከረም 19 ቀን 2013 ዓ.ም ነበር በ90 አመታቸው ከዚህ ዓለም የተለዩት።