የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ለሕዳሴ ግድብ ግንባታ የ20 ሚሊዮን ብር ቦንድ ገዛ

77

አዲስ አበባ፣ መስከረም 27/2014 (ኢዜአ) የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ እንዲውል የ20 ሚሊዮን ብር ቦንድ ግዥ ፈጸመ።

የቦንድ ግዥ ድጋፉን የግድቡ ግንባታ ሕዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ዳይሬክተር ዶክተር አረጋዊ በርሔ ተረክበዋል።

ዳይሬክተሩ ኮርፖሬሽኑ ላደረገው ድጋፍ አመስግነው በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ አገራት የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያውያን የኢትዮጵያ ወዳጆች ድጋፍ እንዲያጠናክሩ ጥሪ አቅርበዋል።

የግድቡን ግንባታ ለማደናቀፍ ከውጭና ከውስጥም የሚደረጉ ጫናዎችን ለመቋቋም በዲፕሎማሲ፣ በእውቀትና በገንዘብ መደገፍ እንደሚገባም አክለዋል።

ለኢትዮጵያ የፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጥያቄ የህወሓት ተላኪዎች፣ ተደራዳሪ እና ምዕራባዊያን አገራት ቀና አመለካከት የላቸውም ነው ያሉት ዶክተር አረጋዊ።

እነዚህን ጫናዎች ተቋቁሞ የግድቡን ግንባታ ለማጠናቀቅ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ድጋፍ የማድረግ ታሪካዊ ሃላፊነት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

የኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ረሻድ ከማል በበኩላቸው ተቋሙ ለአገራዊ ጥሪዎች ፈጣን ምላሽ በመስጠት ለሕዳሴ ግድብ ግንባታ የ20 ሚሊዮን ብር ቦንድ ግዥ መፈጸሙን ገልጸዋል።

ሕዝቡና መንግስት ከምንጊዜውም በላይ አንድነታቸውን በማጠናከር ከውስጥና ከውጭ የተቃጣውን አገር የማፈራረስ እኩይ ዓላማ በመመከት የተጀመረውን ልማት ለማሳካት እያደረጉ ላለው ርብርብ ኮርፖሬሽኑ የበኩሉን እንደሚወጣም ተናግረዋል።

ተቋሙ ባለፈው ዓመትም የ20 ሚሊዮን ብር ቦንድ ግዥ መፈጸሙን አውስተው የግድቡ ግንባታ እስከሚጠናቀቅ ድጋፉ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

በኢትዮጵያዊያን አቅም እየተገነባ ያለው የሕዳሴ ግድብ ግንባታ አፈጻጸም ከ80 በመቶ በላይ መድረሱ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም