መሰረታዊ የግብርና ዘርፍ ለውጥ ለማምጣት የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ነው

177

መስከረም 26/2014 (ኢዜአ) በግብርና ዘርፍ መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣት ምርትና ምርታነት የማሳደግና ሌሎች ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት ሽመልስ አብዲሳ ገለጹ።

በኦሮሚያ ክልል በማህበር ተደራጅተው አቮካዶ በማምረት ለመጀመሪያ ጊዜ ለውጭ ገበያ ማቅረብ ለጀመሩ አርሶ አደሮች እውቅና ተሰጥቷል።

በእውቅና መርሃ ግብሩ ላይ የክልሉ ፕሬዚዳንት ሺመልስ አብዲሳና የግብርና ሚኒስትሩ ዑመር ሁሴን ታድመዋል።

አቶ ሺመልስ በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት በግብርናው ዘርፍ መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣት የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ነው።

ግብርናውን በመስኖ ለመደግፍ ግድቦችና የውሃ ማቆሪያ ኩሬዎች መገንባታቸውንና ለአርሶ አደሮችም የውሃ ፓምፖች መሰጠታቸውን ገልጸዋል።

አርሶ አደሩን የማሰልጠንና የመደገፍ ስራዎች እየተከናወኑ እንደሆነና ይህም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አክለዋል።

በክልሉ በሞጆ፣ በነቀምቴ እና ጅማ ክላስተሮች ዝርያቸው የተሻሻሉ የአቮካዶ ምርቶችን በመስጠት ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ እየተሰራ እንደሆነም ገልጸዋል።

ይህን ተግባር በመቀጠል የምግብ ዋስትና ማረጋገጥና ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በማስቀረት በዘርፉ የስራ ዕድል ለመፍጠር መስራት እንደሚገባም ተናግረዋል።

የግብርናውን ዘርፍ ችግሮች በመፍታት ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግና በአገሪቱ ኢኮኖሚ ውስጥ የጎላ ሚናውን ይዞ እንዲቀጥል ለማድረግ የተለያዩ እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ እንደሆነም ተናግረዋል።

"አርሶ አደራችን ከተደገፈ የበለጠ ማምረት እንደሚችል በተግባር አሳይቶናል፣ ለዓለም ገበያም ምርቱን እያቀረበ ነው" ብለዋል።

የአገሪቷ የጀርባ አጥንት ከሆነው የግብርና ምርት የሚገኘውን ገቢ ማሳደግና የሕዝቡንም ሕይወት ማሻሻል ላይ መስራት እንደሚገባም ነው የገለጹት።

ከአቮካዶ ምርት የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ የክልሉ መንግስት ለአርሶ አደሩ ችግኝ በብዛት በማቅረብ የተሻለ ውጤት መገኘቱን የገለጹት አቶ ሺመልስ ባለፉት ሶሰት ዓመታት ከ660 ሄክታር በላይ መሬት በአቮካዶ ምርት መሸፈኑን ጠቅሰዋል።

የግብርና ሚኒስትሩ ሁመር ሁሴን በበኩላቸው የግብርናውን ዘርፍ ለማሳደግ የተለየ ትኩረት መሰጠቱን ተናግረዋል።

በአትክልትና ፍራፍሬ በለተለይም ለአቮካዶ፣ ለሙዝ እና ለቡና ትኩረት መሰጠቱን ጠቁመዋል።

በምርት ጥራት፣ በኩታ ገጠም እርሻ፣ ምርትን በብዛት ለገበያ ለማቅረብ መንግስት በትኩረት እየሰራ መሆኑንና በጎ ጅምሮችን በማጠናከር የበለጠ እንደሚሰራ ገልጸዋል።

ከአትክልትና ፍራፍሬ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ በአቮካዶ ምርት እየለማ ያለውን 6 ሺህ ሄክታር አካባቢ ማስፋት እንደሚገባም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም