የአዕምሮ ጤና እክል ትኩረት ይሻል

96

መስከረም 26/2014 (ኢዜአ) የአዕምሮ ጤና እክል ከግለሰብ ባሻገር በቤተሰብ ብሎም በአገር የሚያስከተለው ቀውስ ከፍተኛ በመሆኑ ትኩረት እንደሚያሻው ተገለጸ።

በዓለም አቀፍ ደረጃ በአንድ ቤተሰብ ውስጥ ከሚኖሩ አምስት ሰዎች አንዱ የአዕምሮ ጤና እክል ችግሩ ተጠቂ ይሆናል።

የአዕምሮ ጤና ችግር በከፍተኛ ደረጃ ከሚታየው ይልቅ በመካከለኛና ዝቅተኛ በሚካተቱት እንደ ጭንቀት፣ ድብርት፣ እንቅልፍ ማጣት በሰፊው እንደሚስተዋል የኤካ ኮተቤ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የአዕምሮ ሕክምና ባለሙያ ዶክተር ዳዊት አሰፋ ገልጸዋል።

ችግሩ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ያላደጉ አገራት ደግሞ ከፍ ባለ ሁኔታ እንዲሚታይ አንስተዋል።

የኅብረተሰቡ ከእዕምሮ ጤና እክል ጋር ተያይዞ ለዘመናዊ ህክምና ትኩረት አለመስጠት ከችግሩ አባባሽ ምክንያቶች አንደኛው መሆኑን ጠቅሰዋል።

እንደማሳያ ያነሱትም በኢትዮጵያ የአዕምሮ ጤና እክል ካለባቸው መካከል ዘመናዊ ሕክምና ለማግኘት የሚሄዱት ከ10 በመቶ ያልበለጡ መሆናቸውን ነው።

ከእነዚህ ውስጥ ሕክምናቸውን በትክክል የሚከታተሉት ደግሞ አንድ በመቶ ብቻ እንደሆኑ ገልጸዋል።

የአዕምሮ ጤና እክል በግለሰብ ብቻ ሳይሆን በቤተሰብና በአገር ደረጃ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ቀውሱ ከፍተኛ መሆኑንም አመልክተዋል።

በመሆኑም የአዕምሮ ጤና እክል የሚያስከትለውን ተያያዥ ጉዳት ለመቀነስ ግንዛቤ የመፍጠርና አስፈጻሚ አካላትም ትኩረት ሰጥተው መስራት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም