አዲሱ የሚኒስትሮች ምክር ቤት አወቃቀር በኢትዮጵያ የዘመናዊ ፖለቲካ ሒደት ያልታየ አዲስ ምዕራፍ ነው

131

መስከረም 26 ቀን 2014 (ኢዜአ) የጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ የሚመራው አዲሱ የሚኒስትሮች ምክር ቤት አወቃቀር በኢትዮጵያ የዘመናዊ ፖለቲካ ሒደት ያልታየ አዲስ ምዕራፍ የከፈተ መሆኑን የሕግ ምሁራን ገለጹ።

ምሁራኑ አዲሱ ካቢኔ ከአገሪቷ ወቅታዊ ሁኔታ አንፃር የሚታይ ለውጥ እንደሚያመጣ ግምት የሚሰጠው ነው ሲሉም ተናግረዋል።

ዛሬ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፀደቀው የሚኒስትሮች ሹመት በጥንቃቄና አገር በሚያሻግር መልኩ የተሰራ መሆኑን መረዳት እንደሚቻል ገልጸዋል።

የሚኒስትሮቹ ሹመት በአገሪቷ የፖለቲካ ሥርዓት አንዱ ተመልካች ሌላው ፈላጭ ቆራጭ የሚሆንበት ጊዜ አብቅቶ በመንግስት ውሳኔዎች ሁሉም ተሳታፊ የሚሆንበት ሥርዓት መምጣቱን የሚያበስር እንደሆነም ጠቅሰዋል።

የሕግ ምሁሩ አቶ ኤፍሬም ታምራት፤ እስካሁን የነበረው የፖለቲካ አካሔድ ለአውራ ፓርቲ ብቻ መብት የሚሰጥና የመድብለ ፓርቲ ስርዓት ግንባታን የሚያኮስስ እንደነበረ ገልጸዋል።

ገዢው የብልጽግና ፓርቲ በምርጫ አብላጫ ድምጽ ቢያገኝም ካቢኔው እንዲዋቀር ያደረገበት መንገድ ለአገርና ለሕዝብ ጥቅም በጋራ መስራት የሚያስችል በር የከፈተ መሆኑን ጠቁመዋል።

በዋናነትም የሕዝብ ድምጽ ያከበረና ሕዝብን የሚመስል የሚኒስትሮች ምክር ቤት እንዲኖር መደረጉ በአገሪቷ እውነተኛ የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት ግንባታ እየተካሔደ ለመሆኑ ማሳያ እንደሆነ አንስተዋል።

“በቀደሙት መንግሥታት የነበረው የፖለቲካ ሥርዓት አሳታፊ አልነበረም” ያሉት ምሁሩ፤ አዲስ የተመሰረተው መንግስት በጋራ የተገነባች አገር እንድትኖር መደላድሎችን እየፈጠረ መሆኑን እንደሚያሳይ ገልጸዋል።

“የብልጽግና ፓርቲ የተፎካካሪ ፓርቲ አባላት ተሳትፎ እንዲኖር ማድረጉ የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት ያለውን ፍላጎት ያመላክታል” ብለዋል።

ሹመቱ ለቀጣዩ ትውልድ በአገር ጉዳይ በጋራ መስራት እንደሚቻል ልምድ የሚቀመርበት እንደሆነ ጠቁመዋል።

የሕግ ምሁርና ጠበቃ አቶ ቸርነት ኦርዶፋ “ጠቅላይ ሚኒስትሩ ካቢኒያቸውን ያዋቀሩበት መንገድ መንግስት በአገሪቷ ሁለንተናዊ ለውጥ ለማምጣት እያደረገ ያለውን ጥረት አሳይቶናል” ብለዋል።

አዲሶቹ ሚኒስትሮች ያካበቱትን የስራ ልምድ መነሻ በማድረግ ለውጥ ሊያስመዘግቡ የሚችሉ እንደሆኑ ‘አያጠራጥርም’ ብለዋል።

በኢትዮጵያ በሁሉም መስኮች ተጠያቂነት፣ ግልጽነትና ፍትሃዊነትን ለማስፈን በጥንቃቄ እየተሰራ ስለመሆኑ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚኒስትሮች ምክር ቤቱን ያዋቀሩበት ሁኔታ በግልጽ ማስቀመጡን ገልጸዋል።

“በመሆኑም ተሿሚዎቹ ፓርቲ ሳይሆን ኢትዮጵያ አገራቸውን እንደሚያገለግሉ ተገንዝበው መስራት ይጠበቅባቸዋል” ብለዋል።

አገሪቷ ከገጠሟት ውስብስብ ችግሮች እንድትወጣ በተገቢው መንገድ በመስራት የተሰጣቸውን የመሪነት ሚና ዕድል ሊጠቀሙበት እንደሚገባም ጠቁመዋል።