የኢትዮጵን ብልጽግና ለማረጋገጥ ሁሉም ዜጋ የድርሻውን ሊወጣ ይገባል

119

አርባ ምንጭ/ሚዛን አማን፤ መስከረም 26/2014 (ኢዜአ) አዲስ የተመሰረተው መንግስት የኢትዮጵን ብልጽግና ለማረጋገጥ የሚያደርገውን እንቅስቀሴ በመደገፍ ሁሉም ዜጋ የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ ምሁራን ተናገሩ።

የፀጥታ ችግሮችንና የኑሮ ውድነት አሳታፊ በሆነ መልኩ መፍታት ከአዲሱ መንግሥት እንደሚጠበቅም ተመልክቷል።

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር አለማየሁ ጩፋሞ ለኢዜአ እንዳሉት፤  በዴሞክራሲያዊ ምርጫ መንግስት መመስረት መቻሉ ትልቅ እመርታ ነው።

ይህ ደግሞ ኢትዮጵያ ትፈርሳለች ለሚሉ የውስጥና ውጭ ሃይሎች ኢትጵያ በፈተናዎች ውስጥም ቢሆን አሸናፊ ሆና መውጣቷን የሚያሳይ ነው ያሉት።

''አዲሱ መንግስት ብቻውን ለውጥ እንዲያመጣ መጠበቅ የለብንም'' ያሉት ዶክተር አለማየሁ፤ ሁሉም ዜጋ  በተሰማራንበት የሙያ መስክ ውጤታማ ሊሆን እንደሚገባ ጠቁመዋል።

በዩኒቨርሲቲው የታሪክና ቅርስ አስተዳደር ትምህርት ክፍል ምሁር  ካሡ ጡሚሶ በበኩላቸው፤ አዲስ የተሾሙ የካቢኔ አባላት ሀገራዊ ለውጡን ውጤታማ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆን እንዳለባቸው አመልክተዋል።

አዲሱ መንግስት ሰላምና ፀጥታን በማስፈን የኢትዮጵያን ህልውና ለማረጋገጥ ቅድሚያ ሰጥቶ መስራት እንዳለበት ጠቁመዋል።

 ህዝቡም አንድነቱን በማጠናከር የውስጥና ውጭ ጠላቶችን በመመከት ሴራቸውን ለማክሸፍ የበኩሉን መወጣት እንዳለበት ተናግረዋል።

የኑሮ ውድነቱ በህብረተሰቡ የዕለት ከዕለት ኑሮ ላይ ፈተና መሆኑን ያመለከቱት ምሁሩ፤ ሰው ሰራሽ ችግሮችን ፈጥኖ በማስተካከል ረገድ መንግስት ቁርጠኛ ሊሆን ይገባል ነው ያሉት።

ላለፉት 27 ዓመታት ዜጎች  እርስ በርስ እንዳይተማመኑ ያደረገውን አሠራር ከስር መሠረቱ በመንቀል ኢትዮጵያዊነትን ማጉላት እንደሚጠበቅ የተናገሩት ደግሞ  በዩኒቨርሲቲው ሳውላ ካምፓስ የተግባቦትና ሚዲያ ጥናት ትምህርት ክፍል ምሁር  ድረስ ዱማዬ ናቸው።

የህዝባዊ መንግስት ምስረታው በአደባባይ ስነ ሥርዓት መከናወኑ  ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለመላው አፍሪካ ትልቅ ኩራት ነው ብለዋል።

የሚወጡ  ፖሊስና  ስትራቴጅዎች የህዝቡን ፍላጎት መሠረት ያደረጉ መሆን እንዳለባቸው ጠቁመዋል።

ምሁራን የሚያደርጓቸው ጥናትና ምርምሮች ለመንግስት ፖሊስና ስትራቴጂ ግብዓት ሊሆኑ የሚችሉና ችግር ፈቺ  መሆን እንዳለባቸው ጠቅሰው 'ለዚሁም የበኩላቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል።

የሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ  የአስተዳደርና ልማት ጥናት ትምህርት ክፍል ምሁር  ይታገሱ በቀለ፤ ባለፈው ዓመት በብዙ ችግሮች ውስጥ ሆኖ ምርጫው  ማሳካት መቻሉን ተናግረዋል።

አዲሱ መንግስት የጸጥታና የኑሮ ውድነት ችግሮችን ለመፍታት  የመንግስት ቀዳሚ ተግባር መሆኑን ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በሁለቱ ምክር ቤቶች መክፈቻ ስነስርዓት ላይ እንዲሁም ጠቅላይ ሚንስትሩ በበዓለ ሲመታቸው ባደረጉት ንግግር መግለጻቸው ትኩረት ስለመሰጠቱም  አንስተዋል።

በዩኒቨርሲቲው የታሪክ ምሁር አጥናፉ ምትኩ በበኩላቸው፤ በአዲሱ ምዕራፍ ኢትዮጵያን  ወደ ከፍታዋ ለማሻገር የህዝቡን አንድነት ማጠናከር ላይ ትኩረት ተሰጥቶ መስራት እንዳለበት ተናግረዋል።

ችግሮችን ለማለፍና የውጪ ጣልቃ ገብነትን ለመቋቋም ልማትንና  የጸጥታ ሃይልን ለማጠናከር  በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

ቃል ለተገቡ የሰላምና ልማት እንዲሁም የመልካም አስተዳደር የለውጥ ስራዎች ተግባራዊነት ከቀበሌ ጀምሮ ያሉ አስፈጻሚ አካላትና ሀዝቡ የድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አመልክተዋል።

አዲሱ የኢፌዴሪ መንግስት መስከረም 24/2014 ዓ.ም. ሲመሰረት  አቶ ታገሰ ጫፎ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ፣   አቶ አገኘሁ ተሻገር የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ  እና ዶክተር አብይ አህመድን ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ሲሾሙ ዛሬ ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትሩ  ለምክር ቤቱ የቀረቧቸው ሚኒስትሮች/ የካቢኒ አባላት/ ሹመት መጽደቁን በወቅቱ ተገልጿል።

ከዚህ ቀደም ብሎም የኦሮሚያ፣ አማራ፣ ደቡብ፣ ሲዳማ፣ አፋር እና  ጋምቤላ ክልሎች መንግስታት እንዲሁም የአዲስ አበባ እና ድሬዳዋ አስተዳደሮች መመሰረታቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም