ሀገሪቱን ወደ ተሻለ የእድገት ደረጃ ለማሻገር መንግስት የሚያደርገውን ጥረት እናግዛለን

51

ጎባ፤ መስከረም 26/2014 (ኢዜአ) ሀገሪቱን ወደ ተሻለ የእድገት ደረጃ ለማሻገር አዲስ የተመሰረተው የኢፌዴሪ መንግስት የሚያደርገውን ጥረት እንደሚያግዙ በባሌ ዞን የጎባ ከተማ ነዋሪዎች አስታወቁ፡፡

የመንግስት ምስረታው ሂደት ታሪካዊ ብቻ ሳይሆን ለሌሎች የአፍሪካ አገራት ጭምር ምርጥ ተሞክሮ ሊሆን እንደሚችልም ገልጸዋል፡፡

ከነዋሪዎቹ መካከል አቶ አህመድ ናሲር "የመንግስት ምስረታው ግልጽነት የታየበት፣ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት የሰፈነበት በመሆኑ ደስተኛ ነኝ" ብለዋል፡፡

"በተለይ በሀገሪቱ የተጀመሩ ሁለንተናዊ የልማት ውጥኖች ከግብ የሚደርሱትና ሀገር የምትሻገረው የነቃ የህዝብ ተሳትፎ ሲኖር መሆኑን ስለሚረዳ መንግስት የሚያደርገውን ጥረት በመደገፍ የበኩሌን እወጣለሁ" ሲሉም ተናግረዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ኢትዮጵያን ለማሻገር ያላቸው የጸና አቋምና የሚከተሉት የመደመር እሳቤ ሀገሪቱ ከችግር ያወጣታል የሚል እምነት እንዳላቸው የገለጹት ደግሞ ሌላው አስተያየት ሰጪ  አቶ አብረሃም ግርማ ናቸው፡፡

ዕቅዳቸውና ራዕያቸው ከግብ እንዲደርስ በመደገፍ የዜግነት ድርሻቸውን  ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ ሌሎች ተሿሚዎቹ የሀገርን ሰላም በማስፈን የህዝቦችን አንድነት ለማጠናከር በቃለ መሃላ የገቡትን በተግባር ማስመስከር እንደሚጠበቅባቸው አመልክተዋል ፡፡ 

አቶ አማረ መስፍን በበኩላቸው፤  ኢትዮዽያ የውጭ ጣልቃ ገብነትን ተቋቁማ በህዝብ የተመረጠ መንግስት ለመመስረት መብቃቷ ለሉዓላዊነቱ  የማይደራደሩ ኩሩ ህዝብ ያላት መሆኑን በተግባር ያሳየ ነው ብለዋል።

አዲሱ  መንግስትም የውስጥና የውጭ ጫናዎችን በመቋቋም የህዝቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች መልስ እንዲያገኙ ከህዝብ ጋር ተቀራርቦ መስራት እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡

መንግስት ተፎካካሪ ፓርቲዎችን በማሳተፍ  ወደ ስልጣን በማምጣት በኩል የታየው  ጅማሮ መልካም  መሆኑን በመግለጽ እንደሚደግፉ የተናገሩት ደግሞ  አቶ አብዱለጢፍ አህመድ ናቸው፡ 

በተለይ ይህ አካታች የሆነ የመንግስት ምስረታ ሂደት በቀጣይ ለሚደረገው  ብሔራዊ መግባባት ሂደት መደላደል ይፈጥራል ነው ያሉት፡፡

ለሀገር ሰላምና ለህዝቦች አንድነት ብሎም ብልጽግና መሳካት ከመንግስት ጎን ተሰልፈው የድርሻቸውን ለመወጣት እንደሚጥሩ የገለጹት አስተያየት ሰጪዎቹ፤ አዲስ ለተመረጡ አካላትም መልካም የሥራ ዘመን ተመኝተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም