ምክር ቤቱ የፌዴራል አስፈጻሚ አካላትን ሥልጣንና ተግባር ለመወሰን የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ አጸደቀ

240

መስከረም 26/2014 (ኢዜአ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፌዴራል አስፈጻሚ አካላትን ሥልጣንና ተግባር ለመወሰን የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ በአብላጫ ድምጽ አጸደቀ።

በአዋጁ መሰረት 19 የነበሩት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ወደ 22 ከፍ ብለዋል።

ስድስተኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 1ኛ ዓመት የስራ ዘመን 1ኛ ልዩ ስብሰባውን እያካሄደ ነው።

ምክር ቤቱ የፌዴራል አስፈጻሚ አካላትን ሥልጣንና ተግባር ለመወሰን በቀረበውን ረቂቅ አዋጅ ላይ ተወያይቶ በ386 ድጋፍና በአንድ ድምጸ ተአቅቦ በአብላጫ ድምጽ አጽድቆታል።

የጸደቀው አዋጅ አዋጅ ቁጥር 1263 /2014 ነው።

አምስተኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጥቅምት 6 ቀን 2011 ዓ.ም ባደረገው መደበኛ ስብሰባ የፌዴራል መንግሥትን አስፈጻሚ አካላት ስልጣንና ተግባር ለመወሰን የተዘጋጀውን ረቂቅ አዋጅ በሙሉ ማጽደቁ የሚታወስ ነው።

በወቅቱ ምክር ቤቱ የተዘጋጀውን ረቂቅ አዋጅ ቁጥር 961/208 እንደገና በማሻሻል አዋጅ ቁጥር 1097/2011 ሆኖ እንዲጸድቅም አድርጓል።

በጸደቀው አዋጅ የካቢኔ አባላት ከ28 ወደ 20 ዝቅ እንዲሉ የተደረገ ሲሆን፤ በአዋጁ መሰረት 19 ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ተቋቁመው ነበር።

በተሻሻለው አዋጅ ቁጥራቸው 19 የሆኑት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች አዲስ በሚቋቋመው ካቢኔ ወደ 22 ከፍ ይላሉ።

ከተጣመሩትና የአደረጃጀት ለውጥ ከሚያደርጉት ውጭ፣ ወደ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤትነት የመጡት ሁለት ተቋማት ፍትሕ ሚኒስቴር እና የፕላንና ልማት ሚኒስቴር ናቸው።

በካቢኔ አባላት ቁጥር የተደረገው ማሻሻያ ተደራራቢና ድግግሞሽ ሥልጣንና ተግባር የያዙ የመንግሥት ተቋማትን መቀነስ ወይም ለሥራቸው ቅርብ ከሆነ ሌላ የመንግሥት ተቋም ጋር እንዲዋሃዱ ማድረግ ማስፈለጉም ተገልጿል።

ኢትዮጵያ የያዘችውን የለውጥ ጉዞ ለማስቀጠል የሚያስችል አደረጃጀት መከተል እንዲሁም የአስፈጻሚ አካላትን ቁጥር ቀልጣፋ፣ ወጪ ቆጣቢና ውጤታማ ማድረግ የሚሉትም ተጠቅሰዋል።

የፌዴራል አስፈጻሚ አካላትን ሥልጣንና ተግባር ለመወሰን በወጣው አዋጅ የተቋቋሙት 22 ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ከዚህ እንደሚከተለው ቀርበዋል።

1. ግብርና ሚኒስቴር 

2. የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር

3. የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር

4. የማዕድን ሚኒስቴር

5. የቱሪዝም ሚኒስቴር

6. የስራና ክህሎት ሚኒስቴር

7. የገንዘብ ሚኒስቴር

8. የገቢዎች ሚኒስቴር

9. የፕላንና ልማት ሚኒስቴር

10. የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር

11. የትራንስፖርትና ሎጀስቲክ ሚኒስቴር

12. የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር

13. የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር

14. የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር

15. የትምህርት ሚኒስቴር 

16. የጤና ሚኒስቴር

17. የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር

18. የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር 

19. መከላከያ ሚኒስቴር

20. የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

21. የፍትህ ሚኒስቴር እና

22. የሠላም ሚኒስቴር ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም