የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ በሚያካሄው ልዩ ስብሰባ በሦስት ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ ያሳልፋል

171

መስከረም 26/2014 (ኢዜአ)የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ በሚያካሂደው 1ኛ ልዩ ስብስባ በሦስት ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ እንደሚያሳልፍ ምክር ቤቱ አስታውቋል።

ምክር ቤቱ እንዳስታወቀው የአስፈጻሚ አካላትን ሥልጣንና ተግባር መወሰኛ ረቂቅ አዋጅና በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚቀርብለትን የሚኒስትሮች ሹመት መርምሮ ያጸድቃል ተብሎይጠበቃል።በተጨማሪም ምክር ቤቱ በልዩ ስብሰባው ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በሁለቱ ምክር ቤቶች የጋራ መደበኛ ስብሰባ ላይ ያደረጉትን የመክፈቻ ንግግር አስመልክቶ የቀረበውን የድጋፍ ሞሽን እንደሚያዳምጥ ተገልጿል።

ስድስተኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የምስረታ ጉባኤውን ከትናንት ወዲያ ያካሄደ ሲሆን፤ በጉባኤው ዶክተር ዐቢይ አህመድን ጠቅላይ ሚኒስትር አድርጎ መሰየሙ ይታወቃል፡፡በተጨማሪም አቶ ታገሰ ጫፎን የምክር ቤቱ አፈ-ጉባኤ እንዲሁም ወይዘሮ ሎሚ በዶን ምክትል አፈ-ጉባኤ አድርጎ መርጧል፡፡

የፌዴሬሽን ምክር ቤትም በተመሳሳይ ባደረገው የምስረታ ጉባኤ አቶ አገኘሁ ተሻገርን በአፈ-ጉባኤነት፤ ወይዘሮ ዘሃራ ኡመድ አሊን ደግሞ በምክትል አፈ-ጉባኤነት መምረጡ የሚታወስ ነው፡፡