አዲስ አበባ ውስጥ ከአንድ ሺህ በላይ ህገ ወጥ ሽጉጦችና በርካታ ጥይቶች በቁጥጥር ስር ዋሉ

6922

አዲስ አበባ ነሐሴ 11/2010 በህገ-ወጥ መንገድ ወደ አዲስ አበባ የገቡ 1 ሺህ 51 ሽጉጦችንና በርካታ ጥይቶችን በቁጥጥር ሥር ማዋሉን የፌደራል ፖሊስ አስታወቀ።

የፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ የተደራጁና ልዩ ልዩ ወንጀሎች ምርመራ ዳይሬክተር ኮማንደር ከተማ ደባልቄ ዛሬ ለኢዜአ እንደገለጹት የጦር መሳሪያዎቹ በቁጥጥር ስር የዋሉት በህብረተሰቡ ጥቆማ ነው።

ከህብረተሰቡ በተገኘው ጥቆማ መሰረት የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት እና የፈደራል ፖሊስ ባካሄዱት የተቀናጀ ክትትልና ኦፕሬሽን የጦር መሳሪያዎቹ በነዳጅ መጫኛ ቦቴ እና አይሱዙ የጭነት ተሽከርካሪዎች ውስጥ እንዳሉ በቁጥጥር ስር ውለዋል።

የጭነት ተሸከርካሪው አዲሱ ገበያ በተለምዶ ጽዮን ሆቴል አካባቢ 4038 የሽጉጥና ክላሽ ጥይቶችን፣  የነዳጅ ማመላሻ ቦቴው  ደግሞ 1051 ሽጉጦችን  እንደያዙ ኮልፌ አካባቢ በቁጥጥር ስር መዋላቸውንም ነው ኮማንደሩ የገለጹት፡፡

ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ ሶስት ሰዎች በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

በ2010 ዓ.ም ብቻ በርካታ ህገ ወጥ ጦር መሳሪያዎች ወደ አዲስ አበባ ሊገቡ ሲል በፖሊስ መያዛቸውን ኮማንደሩ አስታውሰዋል።

በዛሬው እለት በቁጥጥር ስር የዋሉት መሳሪያዎችና ጥይቶች በደላሎች አማካኝነት ለንግድ አገልግሎት በተለያዩ የአገሪቷ ክፍሎች የሚሰራጩ መሆናቸውንም ኮማንደሩ ተናግረዋል።

በአገሪቷ አንዳንድ አካባቢዎች ግጭት መኖራቸውን ህብረተሰቡ ተገንዝቦ ህገ ወጥ የጦር መሳሪያዎችን ለመከለላከል በሚደረገው ጥረት ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርግ ኮማንደሩ ጠይቀዋል።

ህገ ወጥ የመሳሪያ ዝውውርን ለመግታት ቡድን ተዋቅሮ በጥናት የተደገፈ እርምጃ እየተወሰደ ነው ያሉት ኮማንደሩ ርምጃዎቹ በቀጣይ ለህዝብ ይፋ እንደሚሆኑ ጠቁመዋል፡፡