አቅጣጫውን የሳተ ትኩረት …

685

ኢትዮጵያ ከተልዕኮአቸው ውጪ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ሰባት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) የእርዳታ ሰጪ ድርጅቶች ሰራተኞችን በ72 ሰዓት ውስጥ ከሀገር እንዲወጡ ማድረጓ ይታወሳል፡፡ ይህ እርምጃ ተገቢነት ያለው ቢሆንም በርካቶች ግን ጉዳዩ እንዳሳሰባቸው በመግለጫ ጋጋታ አሰምተዋል።

በ21ኛው ክፍለ ዘመን ላይ ሆነውም የቅኝ ግዛት አባዜ ያለቀቃቸው ሀገራት እና የሰብዓዊ ድጋፍ አቅራቢ ድርጅቶች መሪዎችን እያስጨነቀ የሚገኘው የትግራይ ህዝብን ችግር አይደለም። ይህ ቢሆንማ ኖሮ ለህዝቡ ዕርዳታ ለማጓጓዝ እጅግ አስፈላጊ የሆኑ 428 ተሽከርካሪዎች በሽብር ቡድኑ ቁጥጥር ስር ስለመዋላቸው ጉዳይ በሆነ ነበር። ከዚህ ይልቅ ከዓላማቸው ውጪ የሀገሪቱን ሉዓላዊነት በሚጋፋ መልኩ ስራዎችን ሲሰሩ በመገኘታቸው ከሀገር እዲወጡ የተደረጉ የሰባቱ የዕርዳታ አቅራቢ ድርጅት ሰራተኞች ጉዳይ ሆኖ ታይቷል፡፡

የሰብዓዊ ድጋፍ ስርጭቱ እና ማጓጓዙ ስራ ባልተቋረጠበት፤ ሀላፊዎቹን በኢትዮጵያ የመደቡ ድርጅቶች ጉዳዩን በሚገባ ባልገመገሙበት፤ እውነት ስለ ስራው ተጨንቀው ቢሆን እንኳ ሌሎች ሃላፊዎችን መድበው ማሰራት የሚችሉበት ሰፊ ዕድል ባለበት ሁኔታ ይህን አቋም መውሰድ ተቀባይነት የሌለው ነው። ኢትዮጵያ ከድርጅቶቹ ጋርም ሆነ ከሀገራቱ ጋር በቀደመው የትብብር መንፈስ ለመስራት ዝግጁ መሆኗን በገለጸችበት በዚህ ወቅት የድርጅቶቹ እና የሀገራቱ መሪዎች በጉዳዩ ላይ ይህን ያህል መቆጣት የድርጅቶቹም ሆነ የሀገራቱ ፍላጎት ሰብዓዊ ድጋፍ ማቅረብ ወይስ በሰብዓዊ ድጋፍ ሽፋን የሚፈልጉትን ፖለቲካዊ ተልዕኮ ማስፈጸም የሚል ጥያቄ ያስነሳል፡፡

የሰብዓዊ ድጋፍ አቅራቢ ድርጅት ሰራተኞች ከተቀባይ ሀገር እንዲወጡ ሲደረግ በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የተተገበረ በሚመስል መልኩ ይህን ያህል ጫጫታ ለምን ያስብላል፡፡ እነዚሁ ድርጅቶች እና ሀገራት ካለፉት 2 ወራት ወዲህ ለትግራይ ህዝብ የሰብዓዊ ድጋፍ ቁሳቁስ ጭነው የሄዱ ተሸከርካሪዎች የት እንደገቡ ባልታወቁበት ጊዜ እንኳ ተሸከርካሪዎቹ እንዲመለሱ ለማድረግ ይህን ያህል ጫና ለማሳረፍ አልደፈሩም፡፡

ይህን በተመለከተ በቅርቡ መቀመጫውን ሳን ፍራንሲስኮ ከተማ ያደረገ እና ብላክ አጀንዳ ሪፖርት ላይ በኤዲተርነት የምትሰራው አን ጋሪሰን የተባለች ጋዜጠኛ የተሸከርካሪዎቹ አለመመለስን በተመለከተ እነዚህ የሰብዓዊ ድርጅቶች እና ሀገራት ሊመልሷቸው የሚገቡ ቁልፍ ቁልፍ ጥያቄዎችን ያነሳችበትን ሰፋ ያለ ዘገባ አስነብባለች፡፡

አን ጋሪሰን ላለፈው አንድ ዓመት ገደማ በትግራይ ረሃብ ሊሰከሰት ነው በሚል የፌዴራል መንግስት የሰብዓዊ ዕርዳታ ማቅረብ የሚያስችል ኮሪደር ይፍቀድ ሲሉ የነበሩት የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት ሀላፊዋ ሳማንታ ፓወር ዕርዳታ ጭነው ወደ ክልሉ የገቡ 428 ተሸከርካሪዎች ሳይመለሱ መቅረታቸውን ቢሰሙም ምንም አለማለታቸው አስገራሚ ነው በማለት ተችታለች፡፡

ከሀምሌ መግቢያ ጀምሮ በዓለም የምግብ ፕሮግራም አማካኝነት 466 ዕርዳታ የጫኑ የከባድ ጭነት ተሸከርካሪዎች ወደ ትግራይ ክልል ቢላኩም የተመለሱት ግን 38 ብቻ መሆናቸውን በማስታወስ 428 የሚሆኑት ጠፍተዋል አሊያም ሆን ተብሎ እዛው እንዲቆዩ ተደርገዋል ትላለች። ይህን ሁኔታ ዓለም ያወቀው ቢሆንም በዕርዳታ ማቅረብ ስራ ላይ የተሰማሩም ሆኑ ቀደም ሲል ወደ ትግራይ ዕርዳታ የምናቀርብበት ምቹ ሁኔታ ይፈጠርልን በማልት ሲጮሁ የነበሩት አንዳቸውም ደፍረው የሽብር ቡድኑን ማውገዝ አልቻሉም ትላለች፡፡

ጸሀፊዋ አክላም እነዚህ መኪኖች ከዕይታ ተሰውረዋል እንዳይባል ትናንሽ ፒክ አፕ መኪኖች አይደሉም የሚል ሙግት በማንሳት ጉዳዩን በተመለከተ ቢቢሲ የሚመለከታቸውን የዓለም ምግብ ድርጅትን  ቢጠይቅም በቂ ማብራሪያ መስጠት አለመቻላቸውን ትናገራለች።

የሽብር ቡድኑ ተሽከርካሪዎቹን ለራሱ ተልዕኮ መጠቀሚያ ስለማድረጉ በርካታ መረጃዎች እየተንሸራሸሩ ቢታዩም አሁን እየታየ ያለው የተገላቢጦሹ ነው።  በሽብር ቡድኑ ተሸከርካሪዎቹ ተመልሰው የሚፈለገውን የዕርዳታ ቁሳቁስ ወደ ክልሉ እንዲያጓጉዙ ማድረግ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ከመጨነቅ ይልቅ ከተልዕኮ ውጪ ሲንቀሳቀሱ የተገኙ 7 ሰዎች ከሀገር እንዲወጡ የመደረጉ ጉዳይ ዓለምን ሲያስጨንቅ ይታያል፡፡ ይህ ለሰብዓዊነት ከቆመ ሀገርም ሆነ ድርጅት የሚጠበቅ አለመሆኑን በርካቶች ይገልጻሉ፡፡

እነዚህ ድርጅቶች እና ሀገራት የኢትዮጵያን ሉዓላዊ ሀገርነት ወደ ጎን በመግፋት እነዚህን ሰዎች የማባረር መብት የላትም ሲሉም ተደምጠዋል፡፡ በእነዚህ ድርጅቶች እና ሀገራት ላይ የሚነሳው ትልቁ ጥያቄ የዓለም ምግብ ፕሮግራም የዕርዳታ ቁሳቁሶችን ከተለያዩ የሀገሪቱ መጋዘኖች ወደ ትግራይ መጫን እና ማሰራጨት ባላቆመበት በዚህ ወቅት እነዚህ ሰዎች ተባረሩ ብሎ ይህን ያህል አየር መሙላት ምክንያታዊ አለመሆኑን በርካቶች ይስማሙበታል፡፡

ቀደም ሲል የዓለም ምግብ ፕሮግራም ባልደረባ የሆነ ሰው ለሽብር ቡድኑ አፈ-ቀላጤ ጌታቸው ረዳ የሳተላይት ስልክ ሰጥቶ ድብቅ ተልዕኮውን ሲፈጽም መታየቱ የሚታወስ ነው። ይህን በተመለከተ አን ግሪሰን ተሸከርካሪዎቹ በምድር ውስጥ ተቀብረዋል ካልተባለ በስተቀር ዓለም በቴክኖሎጂ በረቀቀበት በዚህ ጊዜ የዓለም ምግብ ፕሮግራም ከ400 በላይ ግዙፍ የሆኑ ተሽከርካሪዎቹ በምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ እና የአሽከርካሪዎችን ደህንነት ለመከታተል የሚረዳ ቢያንስ የተወሰኑ አሽከርካሪዎች የሳተላይት ስልክ የላቸውም ብሎ ለማመን ይከብዳል ትላለች፡፡

ተሸከርካሪዎቹ የሽብር ቡድኑን አባላት እና ተዋጊዎች ጭነው በተለያዩ አካባቢዎች ሲንቀሳቀሱ የሚያሳዩ በርካታ ቪዲዮዎች እየታዩ ቢሆንም የሽብር ቡድኑ አፈ-ቀላጤ ጌታቸው ረዳ ተሸከርካሪዎቹ መመለስ ያልቻሉት ወደ ትግራይ ሲጓዙ ከኢትዮጵያ መንግስት የተሰጣቸው ነዳጅ መመለሻን ያላካተተ በመሆኑ እንደሆነ በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ሲናገር ተደምጧል፡፡

ይህንን የሽብር ቡድኑን ምላሽ ስሁት የሚያደርገው ሌላው መረጃ ደግሞ ዕርዳታውን እያቀረበ የሚገኘው የዓለም ምግብ ፕሮግራም መሆኑ እየታወቀ ተሸከርካሪዎቹ በቂ መመለሻ ነዳጅ ሳይዙ እንዲጓዙ ያደረገው የኢትዮጵያ መንግስት ነው የሚለውን ኢ-ምክንያታዊ ክስ ይጠቀሳል፡፡

አን ግሪሰን ይህን በተመለከተ ሶስት ዋና ዋና ጥያቄዎችን ለዓለም ምግብ ፕሮግራም አንስታለች። እነርሱም አንደኛ ራሱ የዓለም ምግብ ፕሮግራም ቀደም ሲል ወደ ክልሉ የሰብዓዊ ድጋፍ ጭነው የሄዱ 466 ተሸከርካሪዎች ያለ መመለሻ ነዳጅ እንዲሄዱ ሲደረግ ለምን ዝም አለ? ከእነዚህ ውስጥስ የተመለሱት 38 ተሸከርካሪዎች መመለሻ ነዳጅ ከየት አገኙ? 428 ተሸከርካሪዎች በነዳጅ እጥረት ምክንያት ሳይመለሱ ቢቀሩ እንኳ ከዛ በኋላ የተላኩት 149 ተሸከርካሪዎችንስ እንዴት ካለመጠባበቂያ ነዳጅ ላከ? የሚሉ ናቸው።  ለእነዚህ ጥያቄዎች አጥጋቢ ምላሽ መስጠት አለመቻሉን አን ጠቅሳለች፡፡  

አን በዘገባዋ ጨምራ እንዳመላከተችው የዓለም ምግብ ፕሮግራም ሳይመለሱ ለቀሩት ተሽከርካሪዎች ተገቢውን ማብራሪያ ሳይሰጥ እና እንዲመለሱ ለማድረግ ምንም አይነት ጥረት እና ግፊት ሳያደርግ ባለፈው ሳምንት ተጨማሪ ዕርዳታ የጫኑ 149 ተሽከርካሪዎችን ካለመጠባበቂያ ነዳጅ ወደ ክልሉ መላኩ ብቻ ሳይሆን ከእነዚህ መካከልም አንዳቸውም አለመመለሳቸው በድርጅቱ ላይ ጥያቄ እንዲነሳ ያደርጋል ትላለች፡፡ ድርጅቱ ለአሽከርካሪዎቹ የሰጠው ትኩረት እንዲሁም ስላሉበት ሁኔታ ምንም አለማወቁ እና ለማወቅም ጥረት አለማድረጉ ሌሎች አሽከርካሪዎች ወደ ክልሉ እንዳይሄዱ ፍርሃት እንዲያድርባቸው አድርጓል ስትል ገልጻለች፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት ለትግራይ ህዝብ የሚቀርበው የሰብዓዊ ድጋፍ እንዲቀላጠፍ ካለው ፍላጎት የተነሳ የነበሩትን የፍተሻ ኬላዎች ወደ ሁለት ባሳጠረበት በዚህ ወቅት የሽብር ቡድኑ ለተሸከርካሪዎቹ መመለስ አለመቻል ያቀረበው ምክንያት ተዓማኒነት የሌለው ነው፡፡ የሽብር ቡድኑ በምክንያትነት ካስቀመጣቸው ሰበቦች መካከል አብዛኞቹ አሽከርካሪዎች የትግራይ ተወላጆች በመሆናቸው በየስፍራው የመከላከያ ሰራዊት የሚያደርገው ፍተሻ ስላማረራቸው ተመልሰው ወደ ዕርዳታ መጫኛ አካባቢዎች መመለስ አይፈልጉም የሚል ይገኝበታል፡፡

ይህ የሽብር ቡድኑ ኢ-ምክንያታዊ ምላሽ የሽብር ቡድኑን አንድ ትልቅ ኢ-ህዝባዊነት ባህሪን በግልጽ ያሳያል፡፡ ይኸውም አሽከርካሪዎቹን ቀጥሮ የሚያሰራው የዓለም ምግብ ፕሮግራም ወይም የተሸከርካሪዎቹ ባለንብረቶች ሆኖ ሳለ አሽከርካሪዎቹ የትግራይ ተወላጆች በመሆናቸው ብቻ እንኳ ለትግራይ ህዝብ የሚጓጓዘውን የሰብዓዊ አቅርቦት በምንም አይነት ፈተና ውስጥም አልፈው እንዲያጓጉዙ ማበረታታት ሲገባ ይህን አለማድረጋቸውን እንደማምለጫ ምክንያት ሲጠቀምበት ተስተውሏል፡፡

በዚህም ለትግራይ ህዝብ የዕርዳታ ቁሳቁስ እንዳይደርስ ክልከላ በማድረጉ ተግባር ላይ ይህ የሽብር ቡድን እንዳለበት ማረጋገጫ ነው፡፡ ከትግራይ ህዝብ ወቅታዊ ችግር ይልቅ ተሸከርካሪዎቹ ከትግራይ እንዳይወጡ የፈለገበት ምክንያት እጅጉን የሚያስጨንቀው ይህ ቡድን ተሸከርካሪዎቹ ከትግራይ ያልተመለሱት አሽከርካሪዎቹ ተጨማሪ የዕርዳታ ቁሳቁስ እንዳያጓጉዙ በቂ መጠባበቂያ ነዳጅ ስላልተሰጣቸው እንዲሁም አሽከርካሪዎቹ በሚደረገው ፍተሻ በመማረራቸው ነው በማለት ለትግራይ ህዝብ ደንታ እንደሌለው ከማሳየቱም በላይ ተሽከርካሪዎቹን ለራሱ የሽብር ተግባር እያዋላቸው ስለመሆኑ አመላካች ነው፡፡   

ቀደም ሲል በትግራይ ክልል ያለው ችግር እጅግ እንደሚያሳስባቸው ሲገልጹ የነበሩት እና “አስቸኳይ የሰብዓዊ ድጋፍ የምናቀርብበት ኮሪደር ሊከፈት ይገባል፤ የኢትዮጵያ መንግስት የሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦቱ እንዳይደርስ የሚያደርገውን ያልተገባ እንቅስቃሴ በአስቸኳይ ማቆም አለበት” እያሉ ሲናገሩ የነበሩት ቅድሚያ ለህዝብ ተቆርቋሪ መሆን ነበረባቸው።

እነዚህ ሀገራትና ድርጅቶች እውነት የትግራይ ህዝብ ችግር አስጨንቋቸው ቢሆን ኖሮ በትግራይ ክልል በሽብር ቡድኑ ቁጥጥር ስር ያሉት ተሽከርካሪዎች የሚመለሱበትን ሁኔታ ማመቻቸት ይገባቸው ነበር፡፡ የአሜሪካ ባለስልጣናት እና የተራድኦ ድርጅቶቻቸው እንዲሁም የአውሮፓ ህብረት የሽብር ቡድኑ ተሸከርካሪዎቹን አፍኖ ማስቀረቱ እና ተጨማሪ የዕርዳታ ቁሳቁስ እንዳያመላልሱ ሲያስቀራቸው ትንፍሽ አለማለታቸው ወትሮውንም ሲውተረተሩ የነበረው እና ያን ሁሉ መግለጫ እና ስጋት አለን ጫጫታ ሲያሰሙ የነበረው የሽብር ቡድኑን ከሞት ለመታደግ እንጂ ለትግራይ ህዝብ ተጨንቀው እንዳልነበር በይፋ አሳይተዋል፡፡