"በቀን ስምንት ሰዓት ብቻ በመስራት የትም ልንደርስና ያሰብነውን ልናሳካ አንችልም"

79

መስከረም አዲስ አበባ 25/2014 "በቀን ስምንት ሰዓት ብቻ በመስራት የትም ልንደርስና ያሰብነውን ልናሳካ ስለማንችል ሁላችንም ተጨማሪ ጊዜ ሰጥተን ልንሰራ ይገባል" ሲል ሻለቃ አትሌት ሃይሌ ገብረስላሴ ተናገረ።

ሻለቃ አትሌት ሃይሌ ገብረስላሴ በተለይ ለኢዜአ እንደገለፀው ኢትዮጵያ በሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ መንግስት መመስረት መቻሏ ጫና ለመፍጠር ለሚሹ አገሮች ትልቅ መልዕክት ያስተላለፈ መሆኑን ገልፅዋል።

አዲሱ መንግስት ከመቼውም ጊዜ በላይ በትጋት በመስራት የተጣለበትን አገራዊ ሃላፊነት በብቃትና በላቀ አፈፃፀም መወጣት አለበት ብሏል።

የኢትዮጵያን የልማት እቅድ ለማሳካት በቀን ስምንት ሰዓት ብቻ በመስራት የትም ልንደርስና ያሰብነውን ልናሳካ ስለማንችል ሁላችንም ተጨማሪ ጊዜ ሰጥተን ልንሰራ ይገባል ብሏል ሻለቃ ሃይሌ። 

የመንግስት አካላት ከህዝቡ ጋር ተባብረው ለኢትዮጵያ እድገት መስራትና ወደ አዲስ ምእራፍ ማሸጋገር ይጠበቅባቸዋል ነው ያለው።

ኢትዮጵያዊያን የአገራችንን ህልውና ማስጠበቅ ቀዳሚ ስራችን ሊሆን ይገባዋልም ነው ያለው።

በኢትዮጵያ ላይ ጫና ለመፍጠር ፍላጎት ያላቸው አገራት ቀዳሚ አጀንዳ የራሳቸውን ጥቅም ለማስጠበቅ እና ኢትዮጰያ በተፈጥሮ ሃብቷ እንዳትለማና ከድህነት እንዳትወጣ በእጅ አዙር ቅኝ ግዛት ለመያዝ መሆኑን ጠቅሷል።

እያንዳንዱ ኢትዮጰያዊ ይህንን ሴራ በቅጡ በመረዳት ለአገሩ ህልውና የዘወትር ዘብ ሊሆን ይገባዋል ብሏል።

‘’ኢትዮጵያ ጀምራለች’’ ያለው ሻለቃ አትሌት ሃይሌ ገብረስላሴ፤ ኢትዮጵያ እየተጋፈጠችው ያለው ችግር ይዋል ይደር እንጂ ይፈታል የሚል እምነት እንዳለው ተናግሯል።

የትኛውም አካል በኢትዮጵያ ላይ ጊዜያዊ ችግር ሊፈጥር ይችል የሆናል ፈፅሞ ሊያፈርሳት አይችልም ነው ያለው።

ኢትዮጵያዊያን ከአዲሱ የመንግስት አስተዳደር ጎን በመቆም የአገራችንን ልማት ማስቀጠል፣ ህልውናዋን ማስጠበቅና ሉአላዊነቷን ማስከበር አለብን ብሏል አትሌት ሃይሌ ገብረስላሴ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም