"የአፍሪካዊያን እናት፣ በቅኝ ያልተገዛች የነፃነት ተምሳሌት ኢትዮጵያ"

88

መስከረም 24/2014 (ኢዜአ) "የአፍሪካዊያን እናት፣ በቅኝ ያልተገዛች የነፃነት ተምሳሌት ኢትዮጵያ" - የኬንያው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ።

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በዓለ-ሲመት በአዲስ አበባ በመስቀል አደባባይ በደማቅ ስነ ስርአት ተካሂዷል።

የተለያዩ የአፍሪካ አገራት መሪዎች በመርሃ ግበሩ ላይ በመገኘት ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድና የኢትዮጵያ ሕዝብ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የኬንያ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ "የአፍሪካዊያን እናት፣ በቅኝ ያልተገዛች የነፃነት ተምሳሌት ኢትዮጵያ" ሲሉ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል። 

"ኢትዮጵያ እናታችን ነች፤ እናታችን ሰላም ካጣች ልጆቿ ሰላም ስለማይኖረን የተረጋጋች፣ የበለፀገችና ሰላም የሰፈነባት፣ አብሮነት የነገሰባት ኢትዮጵያን እንሻለን" ብለዋል።

በዚህ ረገድም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በኢትዮጵያ ሰላም የማምጣትና ሕዝቡን አንድ የማድረግ ትልቅ ሃላፊነት አለባቸው ነው ያሉት።

የበለጸገችና ሰላማዊ ኢትዮጵያ ለመፍጠር በሚደረገው ጥረት የኬንያ ሕዝብና መንግስት ከጎናችሁ መሆኑን ላረጋግጥላችሁ እወዳለሁ ብለዋል በመልእክታቸው።

ኬንያ ከአፍሪካውያን ወንድምና እህቶች ጋር በመሆን አህጉሪቷ የራሷን እድል ፈንታ በራሷ እንድትወስን በቁርጠኝነት ትሰራለች ሲሉ አረጋግጠዋል።

የደቡብ ሱዳን ፕሬዝዳን ሳልቫኬር ማሃዲት፤ በኢትዮጵያ ምርጫ ያሸነፋችሁት ሁላችሁም በመሆናችሁ እንኳን ደስ ያላችሁ ብለዋል።

"ኢትዮጵያ እናታችን ናት" ያሉት ፕሬዝዳንቱ "በእናንተ እርዳታ ዛሬ የቆምንበት ቦታ ላይ ደርሰናል" ሲሉ ምስጋና አቅርበዋል።

"እኔ እዚህ የተገኘሁት ለንግግር አይደለም፤ ይልቁንም የኢትዮጵያን ሕዝብና ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይን እንኳን ደስ አላችሁ ለማለት ነው" ብለዋል።

ኢትዮጵያ ለእኛ እናታችን ናት፤ በየዘመናቱ የኢትዮጵያ ህዝብና መሪዎቿ ለደቡብ ሱዳን ሰላምና መረጋጋት ብዙ አግዘውናል ነው ያሉት።

በመሆኑም ደቡብ ሱዳን ያለፈችበት ችግር በኢትዮጵያ እንዲደገም ስለማንፈልግ የውስጥ ችግሯን በሰላም በመፍታት ልማቷን እንድታስቀጥል እንሻለን ብለዋል።

የጅቡቲ ፕሬዝዳንት ኢስማኤል ኦማር ጌሌ ኢትዮጵያ በታሪኳ በብዙ ፈተናዎች ያለፈች አገር ናት፤ አሁን ያለችበትንም ፈተና አልፋ ጠንካራና አሸናፊ ሆና እንደምትወጣ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

ታላቅና አኩሪ ታሪክ ያላት ኢትዮጵያ ለበርካታ የአፍሪካ ሀገራት የፓን አፍሪካን መንገድ ያሳየች መሆኗን አመልክተዋል።

ኢትዮጵያ ለምታደርገው የቀጣይ ምዕራፍ ጉዞ የጅቡቲ ሕዝብና መንግስት እንደሚደግፍም አመልክተዋል።

በቀጠናው ያለው የሰላም ሁኔታ ያልተረጋጋ ቢሆንም የሚገጥሙንን ችግሮች በጋራ በመዋጋት የሚከፋፍሉንን ጉዳዮች በጋራ በማስወገድ በድል አብረን ወደፊት እንጓዛለን ብለዋል።

የዩጋን ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ በአፍሪካ የፖለቲካ እይታ ወስጥ ባለፉት 60 አመታት በርካታ ጉዳዮችን መታዘባቸውን ተናግረው የአፍሪካ ትልቁ ችግር የማንነት ፖለቲካ እንደሆነ አመልክተዋል።

"እኔ የወጣሁት ከዚህ ነገድ ነው፣ የምከተለው ሃይማኖት ይሄ ነው በማለት የምንከተለው አካሄድ ወደ ኋላ አስቀርቶናል" ብለዋል፡፡

"ኢትዮጵያም ከማንነት ፖለቲካና ከፍላጎት ፖለቲካ አንዱን መምረጥ አለባት" ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ሙሐመዱ ቡሐሪ ስድስተኛው አጠቃላይ ምርጫ ኢትዮጵያውያን ለዴሞክራሲ መርሆዎች ተገዢ መሆናቸውንና በድምጻቸው ለውጥ እንደሚፈልጉ ያሳዩበት እንደሆነ ገልጸዋል።

ናይጄሪያ የኢትዮጵያ አንድነትና የግዛት አንድነት እንዲከበር ድጋፍ እንደምታደርግ አመልክተዋል።

ቀጣዩ ጊዜ በኢትዮጵያ በናይጄሪያ መካከል ያለው የሁለትዮሽ ግንኙነት ይበልጥ የሚጎለብትበት እንዲሆን እመኛለሁ ብለዋል።

የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሞሐመድ አብዱላሂ ሞሐመድ ኢትዮጵያውያን በስድስተኛው አጠቃላይ ምርጫ የጋራ ራዕያችንና ሕልማችንን ያሳካል ብለው የሚያምኑበትን መንግስት መምረጣቸውን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያና ሶማሊያ በጋራ መከባበር የተመሰረተ ለረጅም ዘመናት የቆየ ግንኙነትና ትስስር አላቸው ያሉት ፕሬዝዳንቱ አገራቱ ዓለም አቀፍ ሽብርተኝነትን ለመዋጋት በጋራ እየሰሩ ነው ብለዋል።

በቀጣይም አገራቱ በተለያዩ መስኮች ያላቸው ግንኙነት ይበልጥ ይጎለብታል ብለው እንደሚያምኑም ተናግረዋል።

የአፍሪካ አገራት መሪዎች ከሕዝባቸው ጋር በትብብር የሚሰሩ እንዲሁም ለዜጎች የጋራ ህልም መሳካት ከተጉ አፍሪካን የሚያቆማት የለም ብለዋል።

የሴኔጋል ፕሬዝዳንት ማኪ ሳልና የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ጠቅላይ ሚኒስትር ጂን-ሚሼል ሳማ ሎኮንዴ ለጠቅላይ ሚኒስቴር ዐቢይ አህመድና ለኢትዮጵያ ሕዝብ እንኳን ደስ አላችሁ ያሉ ሲሆን፤ ለአዲሱ መንግስት መልካም የስራ ጊዜን ተመኝተዋል።

የአፍሪካ አገራት መሪዎች ኢትዮጵያ የበለጸገችና ሰላማዊ የአፍሪካ ቀንድ ለመፍጠር የጀመረችውን ጥረት እንደሚደግፉና ለስኬቱም በጋራ እንደሚሰሩ በመልዕክታቸው ላይ ገልጸዋል።

በመስቀል አደባባይ በተካሄደው የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በዓለ ሲመት ላይ ለመታደም የተለያዩ አገራት መሪዎች፣ የአፍሪካ ሐብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋቂ መህመት፣ የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) ዋና ጸሐፊ ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ፣ የመንግስት ባለስልጣናትና ከተለያዩ አካባቢዎች የመጡ የህብረተሰብ ክፍሎች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም